በድሬዳዋ አስተዳደር በዛሬው እለት በይፋ የተመረቀው ደረጃውን የጠበቀ የጽኑ ህሙማን እና የውስጥ ደዌ ህክምና ክፍል የህብረተሰቡን የጤና አገልግሎት ጥራት በማሳደግ ረገድ ጉልህ ድርሻ እንዳለው ተገልጿል።
በመርሃ ግብሩም ንግግር ያደረጉት የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ክብር አቶ ከድር ጅሀር በዛሬው እለት የተመረቁ የህክምና መስጫ ክፍሎች እንደ ሀገር የተጀመረውን የጤና ዘርፍ የትራንስፎርሜሽን እቅድ የሚያሳኩ መሆኑን ገልጸዋል።
የሳቢያን ጠቅላላ ሆስፒታል የህክምና አገልግሎቱን ከጊዜ ወደ ጊዜ በማስፋት የነዋሪውን ህብረተሰብ የጤና አገልግሎት ጥራት እና ተደራሽነትን በማረጋገጥ ዘርፈ ብዙ ስራዎች ተሰርተዋል።
በቀጣይም በጤናው ዘርፍ የተጀመረውን ሪፎርም ለመደገፍ በትኩረት እንደሚሰራም ነው ከንቲባ ከድር ጅሀር ያስታወቁት።
የድሬደዋ አስተዳደር ጤና ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር ጽጌረዳ ክፍሌም በበኩላቸው መንግስት በሽታን በመከላከል እና የህክምና አገልግሎትን ለማስፋፋት እየሰራ መሆኑን አመልክተዋል።
ሆስፒታሉ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ከመደራጀቱ በተጨማሪ የሚሰጡ የህክምና አገልግሎቶችን በማስፋፋት ደረጃውን የጠበቀ የህክምና አገልግሎት እንዲሰጡ በማደረግ በኩል በርካታ ጥረት መደረጉን ተናግረዋል።
በዚህም በሆስፒታሉ በክቡር ከንቲባ ከድር ጅሀር ኢንሼቲቭ የተጀመረውን የዲያሌሲስ የህክምና አገልግሎቶች እና ሌሎች የህክምና ክፍል ማስፋፊያ በማጠናከሩ ተግባር የመንግስትና የግል ዘርፉ አጋርነትን ለማሳደግ የሚያስችሉ ተግባራት እንደሚከናወኑ ጠቁመዋል።
የተመረቀው የጽኑ ህሙማን እና የውስጥ ደዌ ህክምና ክፍል 10 ክፍሎች ያሉት እና ተላላፊ የሆኑ በሽታዎችን ለመቆጣጠር የሚስች ዘመናዊ መሳሪያ የተገጠመለት ህክምናዎችን በልዩ መልኩ ይሰጣል ተብሏል።


