የድሬዳዋ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ ዋና አዛዥ እና የድሬዳዋ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ኮሚሽነር ዓለሙ መግራ የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ለአፍሪካ ዋንጫ በማለፉ የተሰማቸውን ደስታ በመግለፅ ለመላዊ ኢትዮጵያውያን የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
ብሄራዊ ቡድኑ ከ22 ዓመታት በኋላ ለአፍሪካ ዋንጫ ማለፉ ለዘርፉ ከፍተኛ ትኩረት ተሰቶ በመሰራቱ የተገኘ ድል መሆኑን ኮሚሽነር አለሙ ገልፀው፤ የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ለአፍሪካ ዋንጫ ማለፉ በየክልሎች የሚከናወኑ ከ17 አመት በታች የስፖርት እንቅስቃሴዎችን በከፍተኛ ደረጃ እንደሚያነቃቃ ተናግረዋል።
ኮሚሽነር አለሙ አያይዘውም የሴካፋ ከ17 ዓመት በታች የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ውድድር የምድብ ሁለት ጨዋታዎች በድሬዳዋ ኢንተርናሽናል ስታዲየም ካለምንም የፀጥታ ችግር ፍፁም ሰላማዊ በሆነ መልኩ ሲካሄድ መቆየቱን ገልፀው፤ ለዚህም የበኩላቸውን አስተዋፆ ላበረከቱ አካላት በሙሉ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን በተሰጠ አቅጣጫ መሰረት በድሬዳዋ ከ17 ዓመት በታች በፕሮጀክት ታቅፈው ያሉ ወጣቶችን በአዲስ አደረጃጀት የማደራጀት ስራ እንደሚሰራ የተናገሩት ኮሚሽነሩ ለዚህም የድሬዳዋ ወጣቶች እና ታዳጊዎች በአግባቡ ዝግጅት እንዲያደርጉና በሚደረጉ ውድድሮችም የነቃ ተሳትፎ እንዲያደርጉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
በመጨረሻም ኮሚሽነር አለሙ ከሀረሪ ክልል ጋር በጋራ በመሆን የምስራቅ ኢትዮጵያ የእግር ኳስ ጨዋታን የማስፋፋት እና የማጠናከር ስራ እንደሚሰራ እንዲሁም በቀጣይ የምስራቅ ኢትዮጵያ አጎራባች ክልሎችን በእግር ኳስ የማስተሳሰር ስራ በርብርብ እና በቅንጅት እንደሚሰራ አመላክተዋል።


