በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ 21ኛ ጊዜ በሀገራችን ደግሞ ለ6ኛ ጊዜ “በተቀናጀ ዘዴ
ለህፃናት ህይወት” በሚል የሳንባ ምች ቀን ከጤና ጥበቃ እንዲሁም ከተለያዩ ክልሎች የተወጣጡ እንግዶች በተገኙበት በድሬዳዋ አስተዳደር ተከብሯል።
በዚህም በመርሃ-ግብሩ የተገኙት የአስተዳደሩ ጤና ቢሮ ተወካይ አቶ አቤል ሽፈራው የሳንባ ምች በዓለም ዙሪያ በተለይም ህፃናትን እና እድሜያቸው የገፉ የህብረተሰብ ክፍሎችን ጨምሮ በርካታ ሰዎችን የሚያጠቃ በሽታ መሆኑን ገልፀው በሽታውን ለመከላከል ርብርብ ማደረግ እንደሚገባ አመላክተዋል።
አቶ አቤል አያይዘውም በሽታው ከ5 ዓመት በታች የሆኑ ህፃናትን ለሞት የሚዳርግ በመሆኑ ትኩረት ተሰጥቶ መከላከሉ ላይ ተከታታይ ስራዎች መስራት እንደሚጠይቅ ገልፀዋል።
የኢፌዴሪ ጤና ሚኒስቴር የእናቶችና ህፃናት ዋና ስራ አስፈፃሚ ዶ/ር ማርያማዊት አስፋው በበኩላቸው በዛሬው እለት በሽታውን ለመከላከል መሰራት የሚገባቸው ስራዎች ላይ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት መደረጉን ተናግረው፤ በሽታውን በቀላሉ ለመከላከል የህፃናትን መደበኛ ክትባት ስራ ማጠናከር ፣ግንዛቤዎችን አጠናክሮ በማስቀጠልና በጋራ መስራት የሚጠይቅ መሆኑን ገልፀዋል ።
ዶ/ር ማሪያማዊት አያይዘውም በአስተዳደሩ በጎሮ ጤና ጣቢያ እየተሰጠ ያለውን የተቀናጀ የህጻናት ህክምና እና ክትባት አገልግሎት እንዲሁም በህጻናት ሁለንተናዊ እድገት ላይ እየተሰሩ ያሉ ስራዎች ላይ ልምድ ልውውጥ መደረጉን የተናገሩ ሲሆን በአጠቃላይ በአስተዳደሩ በሽታውን ለመከላከል እየተሰሩ የሚገኙ ስራዎች አበረታች መሆናቸውን ተናግረዋል።
በመርሃ-ግብሩ የሳንባ ምች ምንነትና ጉዳት ላይ ያተኮረ ፅሁፍና የክልሎች ሪፖርት ቀርቧል።


