”በመደመር መንግስት ዕይታ የዘርፎች እመርታ” በሚል መሪ ሀሳብ ሲሰጥ በነበረው የስልጠና ማጠቃለያ ላይ ክቡር የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚንስትር ዶ/ር አብይ አህመድ በሠጡት የስራ አቅጣጫዎች መሠረት በተመረጡ ዘርፎች ላይ ተግባራዊ የሚደረግ የ100 ቀን እቅድ በድሬዳዋ አስተዳደር የተዘጋጀ ሲሆን፤ በዛሬው ዕለት እቅዱን ወደ ስራ ለማስገባት ከአስተዳደሩ አመራሮች ጋር ውይይት ተካሂዷል።
በዚህም በመድረኩ የድሬዳዋ አስተዳደር ብልፅግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ኢብራሂም ዩሱፍ ትኩረት በተሰጣቸው በአራቱ ዋና ዋና ዘርፎች በኢንደስትሪ፣ በግብርና፣ በከተማ ልማት እና በቱሪዝም ዘርፎች እንዲሁም በአጠቃላይ በአስተዳደሩ በ100 ቀናት ሊሰሩ የታቀዱ ስራዎችን አቅርበው ውይይት ተደርጎበታል።
በዚህም ክቡር ከንቲባ አቶ ከድር ጁሀር ዕቅዱን በተቀመጠው የጊዜ ሰሌዳ መሰረት ለማጠናቀቅ በቁርጠኝነት ርብርብ ማድረግ እንደሚገባ የተናገሩ ሲሆን፤ የስራዎች ሂደት በየጊዜው እንደሚገመገምም አመላክተዋል።
በዕቅዱ መሰረት የድሬዳዋን የልማት ግስጋሴ የማፋጠን፣ የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን የመመለስ እና በአጠቃላይም የማህበረሰቡን እርካታ የመጨመር ስራ እንደሚሰራ ከንቲባ ከድር አብራርተዋል::
ክቡር ከንቲባ ከድር አያይዘውም በከተማም በገጠርም ለሚገኙ ወጣቶች በተለያዩ ዘርፎች የስራ እድል የመፍጠሩ ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የገለፁ ሲሆን ከተረጂነት ለመላቀቅና ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ እየተሰሩ የሚገኙ ስራዎችን አጠናክሮ የማስቀጠል ስራ እንደሚሰራም ጠቁመዋል።
የድሬዳዋ አስተዳደር ክቡር ምክትል ከንቲባ አቶ ሀርቢ ቡህ በበኩላቸው ለታቀደው ዕቅድ መሳካት ሁሉም አመራር በመፍጠን እና በመፍጠር በቁርጠኝነት ሊሰራ እንደሚገባ የጠቁሙ ሲሆን፤ አንዳንድ ስራዎች ረጅም ጊዜ የሚወስዱና በ100 ቀናት ውስጥ የማይጠናቀቁ በመሆናቸው በእቅዱ ላይ የስራዎቹን አፈፃፀም ለማሳካት በተቀመጠው ፐርሰንት መጠን ስራውን ማጠናቀቅ እንደሚገባ አብራርተዋል።
አሁን ላይ በከተማ ወረዳዎች የተጀመሩ የኮሪደር ልማት ስራዎች አበረታች መሆናቸውን ያመላከቱት ደግሞ የድሬዳዋ አስተዳደር ብልፅግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ኢብራሂም ዩሱፍ ሲሆኑ በቀጣይ ይህንን ተሞክሮ በማስፋት በአራቱም የገጠር ክላስተሮች ሞዴል የገጠር ኮሪደር መንደር እንደሚሰራ ተናግረዋል።
አቶ ኢብራሂም አያይዘውም በህገ-ወጥ መልኩ የዋጋ ጭማሪ የሚያደርጉና ምርትን ካለአግባብ በማከማቸት ገበያ ላይ እጥረት እንዲፈጠር የሚያደርጉ ነጋዴዎች ላይም በተጠናከረ መልኩ የቁጥጥር ስራ እንደሚሰራ ጠቁመዋል።


