የድሬዳዋ አስተዳደር የሥራ፣ ክህሎትና ቴክኖሎጂ ቢሮ ክህሎት መር የወጣቶች የሥራ ዕድል ፈጠራን ለማሳደግ እየሰራ መሆኑን አስታወቀ::

የድሬዳዋ አስተዳደር የሥራና ክህሎት ቢሮ በ 100 ቀናት ዕቅድ በምግብ ዋስትና እና በምርት ዘርፍ የሥራ ዕድል ፈጠራን ለማሳደግ በትኩረት እየሰራ መሆኑን

የቢሮው ኃላፊ አቶ ሮቤል ጌታቸው ገልጸዋል።

በዶሮ እርባታ፣ በማር ምርት እና በመንገድ ዳር ፈጣን ምግቦች (Street Food) ዝግጅት ላይ የሚሰማሩ አምስት ማህበራት መደራጀታቸውን አቶ ሮቤል አመላክተው በቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች አማካኝነት ዘመናዊ የንብ ቀፎዎች፣ የዶሮ ቤቶች፣ የዶሮ መኖ ማቀነባበሪያ ማሽኖች እና የከተማዋን ውበት በሚመጥን ሁኔታ ዘመናዊ የጎዳና ላይ ምግብ መሸጫ ጋሪዎች በፈጠራ ዘምነውና እርስ በርስ ተመጋጋቢነት እንዲኖራቸው ተደርገው መሰራታቸውን ጠቁመዋል።

ዘመናዊ የንብ ቀፎ በወጣቶች ለተደራጁ ኢንተርፕራይዞች የስራ ክህሎትና ቴክኖሎጂ ቢሮ ከግብርና ውሃ መአድንና ኢነርጂ ቢሮ ጋር በመሆን የሚያከፋፍል መሆኑንም አቶ ሮቤል ተናግረዋል።

አቶ ሮቤል አያይዘውም ቢሮው በከተማ እርስ በርስ ተመጋጋቢ የሆኑ ሶስት እንዲሁም በገጠር ሁለት በድምሩ አምስት አዳዲስ ኢንተርፕራይዞችን ስራ በማስጀመር የስራ አጥነትን ቁጥር መቀነስን ትኩረት ያደረገ ስራ በማከናወን ላይ እንደሚገኝ ያብራሩ ሲሆን ኢንተርፕራይዞቹ የሚጠቀሙባቸው ማሽነሪዎችና የፈጠራ ውጤቶች በቢሮው ስር ባሉት ሁለቱ የመንግስት ኮሌጆች በራስ አቅም ፈጠራ ታክሎባቸው የተመረቱ መሆናቸውን አመላክተዋል።

ቢሮው በስሩ የሚገኙ ሁለት የመንግስት ኮሌጆችና ስድስት የግል ኮሌጆች ውስጥ የሚሰሩ ሰባት ሺህ ሶስት መቶ አርባ ስድስት ሰራተኞች ሙሉ በሙሉ ፋይዳ ብሔራዊ መታወቂያ ተጠቃሚዎች መሆናቸውን ኃላፊው ገልጸው በቢሮውም ሆነ በኮሌጆቹ አገልግሎት ለማግኘት የሚመጡ ተገልጋዮች የፋይዳ መታወቂያ መያዝ እንደሚገባቸው አመላክተዋል።

በሌላ በኩል፣ የቴክኖሎጂ ክህሎትን ለማሳደግ እየተተገበረ ባለው የኢትዮ ኮደርስ (Ethio Coders) ፕሮግራም፤ በኢትዮ-ጣልያን እና በድሬዳዋ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ የሚገኙ ሰራተኞችና ተማሪዎችን ጨምሮ 2,600 ሰዎችን ለማሰልጠን ታቅዶ እስካሁን ከ2,500 በላይ ሰልጣኞች ስልጠናውን በመከታተል ላይ እንደሚገኙ አቶ ሮቤል ተጠቁመዋል::

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *