“የከተሞች የምግብ ዋስትና ፕሮግራም ዜጎች ከነበሩት ዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ በመላቀቅ አምራች እና ምርታማ ዜጋ እንዲሆኑ በር የከፈተ ነው”:-የድሬዳዋ አስተዳደር ክቡር ምክትል ከንቲባ አቶ ሀርቢ ቡህ

የከተሞች የምግብ ዋስትና ፕሮግራም ዜጎች ከነበሩት ዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ በመላቀቅ አምራች እና ምርታማ ዜጋ እንዲሆኑ በር የከፈተ ነው ሲሉ የድሬዳዋ አስተዳደር ክቡር ምክትል ከንቲባ አቶ ሀርቢ ቡህ ተናገሩ።

“ከተረጂነት ወደ አምራችነት” በሚል መሪ ሀሳብ የድሬዳዋ አስተዳደር የከተማ ስራ አስኪያጅ ጽ/ቤት የከተማ ልማታዊ ሴፍቲኔት እና የስራ ፕሮጀክት (UPSNJP) የ1ኛ ዙር አዲሽናል ፋይናንስ ተጠቃሚዎች ምርቃት መርሀ-ግብር ተካሂዷል።

በዚህም በመርሃ ግብሩ የተገኙት ክቡር ምክትል ከንቲባ አቶ ሀርቢ ቡህ ለተመራቂዎች የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክታቸውን በማስተላለፍ፤ የፕሮግራሙ ተጠቃሚ ወገኖች ይህን ምቹ አጋጣሚ እንደ ችግር መፍቻ ቁልፍ በመጠቀም የኑሮ ደረጃን ለማሻሻል እና ለሀገር እድገት ተደማሪ አቅም ለመፍጠር ይበልጥ መንቀሳቀስ ይገባቹሀል ሲሉ ተናግረዋል።

የመደመር መንግስት የዜጎች ህይወት ተለውጦ በማህበራዊ እና ምጣኔ ሀብታዊ እድገት ላይ ተደማሪ ውጤት እንዲያበረክቱ በርካታ ድጋፍ እና እገዛ በማድረግ ላይ እንደሚገኝ ክቡር ም/ከንቲባ ሀርቢ አመላክተው፤ የመንግስት ዘርፈ ብዙ ጥረቶችም ስር የሰደዱ ችግሮች እንዲፈቱና ሁለንተናዊ ብልጽግና በሀገሪቱ እንዲረጋገጥ ማስቻል መሆኑን ተናግረዋል።

ም/ከንቲባ ሀርቢ አያይዘውም የተጀመረውን ጥረት ዳር ለማድረስ ከሚያግዙ ፕሮግራሞች መካከል አንዱ የከተሞች የምግብ ዋስትና ፕሮግራም በዋነኝነት እንደሚጠቀስ ጠቁመው የከተሞች የምግብ ዋስትና ፕሮግራም ዜጎች ከነበሩት ዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ በመላቀቅ አምራች እና ምርታማ ዜጋ እንዲሆኑ በር በመክፈት ነገን የተሻለ ኑሮ እንዲመሩና ወደ ብልጽግና እንዲሸጋገሩ የሚያስችል መሆኑን ገልፀዋል።

ለምርቃት የበቁት 342 ቤተሰቦች እና 1191 ተጠቃሚ ያደረገ ይህ ፕሮጀክት በሁለት ዙር ለእያንዳንዱ አባወራ እና እማወራ ከ66 ሺ ብር በላይ ባጠቃላይም ከ22 ሚሊዮን ብር በላይ ለስራ ማስጀመሪያ የገንዘብ ድጋፍ መደረጉን ም/ከንቲባ ሀርቢ ተናግረዋል።

በመጨረሻም ም/ከንቲባ ሀርቢ ተመራቂዎች ባገኛችሁት ስልጠና፣ የምክርና የድጋፍ አገልግሎትን ጨምሮ ያላችሁን ጥሪት ስራ ላይ በማዋል የኑሮ ደረጃችሁን በማሻሻል ከራሳችሁ እና ከቤተሰባችሁ ባለፈ እንደ ዜጋ ለሀገር እድገት በጎ አስተዋጾ ማበርከት ይገባቹሀል በማለት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

የድሬዳዋ አስተዳደር ከተማ ስራ አስኪያጅ ጽ/ቤት ኃላፊ ኢንጂነር ጀማል ኢብራሂም በበኩላቸው የከተማ ልማታዊ ሴፍቲኔትና ፕሮጀክት በሀገር አቀፍና በከተማችን ከ2009 ጀምሮ ተግባራዊ እየተደረገ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

ኢንጂነር ጀማል አያይዘውም መንግስት ከተረጂነት ወደ ምርታማነት በሚል ዜጎች ከራሳቸዉ አልፎ ለሀገር እንዲተርፉ ከፍተኛ ትኩረት አድርጎ እየሰራ እንደሚገኝ የተናገሩ ሲሆን፤ ተመራቂዋች ከተረጂነት ወደ ምርታማነት በመግባት ለሌሎች የስራ እድል በመፍጠር ለሀገር የኢኮኖሚ እድገት የበኩላቸዉን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *