የዘንድሮ ዘመን መለወጫ የበዓል ገበያ ፍትሀዊ ዋጋ እንደታየበት ነዋሪዎች ተናገሩ በአስተዳደራችን ባሉ የገበያ ስፍራዎች ውስጥ ለበዓል የምግብ ፍጆታ የሚሆኑ መሰረታዊ ነገሮችን ሲገበያዩ ያገኘናቸው የከተማችን ነዋሪዎች እንደገለጹት የዘንድሮው የዘመን መለወጫ በዓል ካምናው ጋር ሲነጻጸር በአቅርቦትም ሆነ በዋጋ የተሻለ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ወ/ሮ እመቤት ሞገስ በቀፊራ የገበያ ስፍራ ሲሸምቱ ያገኘናቸው አስተያየት ሰጪ እንደተናገሩት በአውደ አመት አብዛኛውን ጊዜ የምግብ ፍጆታዎች በተለይ እንደ ዶሮ ፣፣ሽንኩርትና ቲማቲም የመሳሰሉት የዋጋ መናር ይስተዋልባቸው የነበረ ቢሆንም በዘንድሮ አመት ግን ዋጋቸው ተመጣጣኝ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ነገር ግን አስተያየት ሰጪዋ እንዳሉት በገበያ ቦታዎች ላይ ያለው ትርምስ የኮሮና ወረርሽኝን እንዳያስፋፋ ስጋት እንዳለባቸው ተናግረዋል፡፡ ሌላው አስተያየት ሰጪ አቶ ቢኒያም በጀላባ አካባቢ ፍየል በመግዛት ላይ ያገኘነው ሲሆን ዋጋው ብዙም ያልተጋነነ እንደውም ቅናሽ ማግኘቱን ተናግሮ የገበያ ቦታው ግን ማህበራዊ ርቀትን ሊያስጠብቅ የማይችልና እርስ በርስ ንክኪ እንዲኖር የሚያስገድድ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ገበያተኛውም በከፊል አፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭንብል እንደማያደርግና ይህም የኮሮናን ቫይረስ ወረርሽኝ ለማስፋፋት አይነተኛ መንስኤ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ አስተያየት ሰጪዎቹ እንደተናገሩት መጪውን ዘመን በጤና ለመኖር ዛሬ ላይ የምናደርገው ጥንቃቄ ወሳኝ በመሆኑ መላው ህብረተሰብ ከኮረና ወረርሽኝ እራሱን በመጠበቅና ለሌላ ሰው በበሽታው መያዝ ምክንያት ባለመሆን በአሉን በጥንቃቄ እንዲያሳልፍ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል ፡፡
የዘንድሮ ዘመን መለወጫ የበዓል ገበያ ፍትሀዊ ዋጋ እንደታየበት ነዋሪዎች ተናገሩ::


