የአንበጣ መንጋው በአራቱ የገጠር ክላስተሮች ላይ እያደረሰ ያለውን ጉዳት የአስተዳደሩ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች በመዘዋወር በአርሶና አርቦቶ አደሩ ላይ የደረሰውን ጉዳት የተመለከቱ ሲሆን አስተዳደሩ የአንበጣ መንጋውን የመከላከል ስራዉን አጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
ከንቲባ አህመድ መሀመድ ቡህ በዋሂል ክላስተር የሚገኙ ቀበሌዎችን ከካቢኔ አባላት ጋር በመሆን ተዘዋውረው የተመለከቱ ሲሆን የተከሰተውን የአንበጣ መንጋ ለመከላከል በአስተዳደሩ ሲደረግ የነበረውን ጥረት አሁንም አጠናክረን በመቀጠል የጉዳት መጠኑን ለመቀነስ እንሰራለን ብለዋል ።
ከንቲባው አክሎም የጉዳት መጠኑ ታይቶ ከፌደራል መንግስት ጋር ተባብረን ለተጎዱት አርሶና አርብቶ አደሩን እንደግፋለን ብለዋል፡፡ከዚህ በፊትም በመንግስት የአንበጣ መንጋውን ለመከላከል የተለያዩ ጥረቶችን እያደረገ ከነበረው ጎን ለጎን ህብረተሰቡ እያደረገ ያለውን በባህላዊ መንገድ የመከላከል ዘመቻ አጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ሲሉም አሳስበዋል።
የአንበጣ መንጋው በዋሂል ክላስተር በተለያዩ ቀበሌዎች በሚገኙ የደረሱ የማሽላ ሰብሎች ጉዳት ያደረሰ ሲሆን የጉዳት መጠኑ ከዚህ በላይ እንዳይሆን አስተዳደሩና ህብረተሰቡ ርብርብ በማድረግ የአንበጣ መንጋውን መከላከል እንዳለበት ተጠቁሟል፡፡
በመስክ ምልከታው ላይ የአስተዳደሩ ፋይናንስና ኢኮኖሚ ቢሮ ሀላፊ አቶ ሱልጣን አልዬ ፣ የጤና ቢሮ ሀላፊ ወ/ሮ ለምለም በዛብህ ፣ የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ሀላፊ አቶ እዝቅያስ ታፈሰ ፣ የአስተዳደሩ መሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ ሀላፊ አቶ ገበየሁ ጥላሁን እና የድሬዳዋ ብልፅግና ፓርቲ ጽ/ቤት የሥራ ኃፊዎች ተገኝተዋል።


