ምክትል ከንቲባና የንግድ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኃላፊ አቶ ከድር ጁሃር ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር የአእምሮ ጤና በየትኛውም የዕድሜ ክልል ከህፃናት እስከ አዋቂ ሁሉንም የማህበረሰብ ክፍል የሚመለከትና ወሳኝ የጤና ጉዳይ በመሆኑ አስተዳደሩ ለጉዳዩ ትኩረት በመስጠት በ2012 ዓ/ም በድል ጮራ ሪፈራል ሆስፒታል ለሚገነባው የህክምና ማዕከል 1.5 ሚሊዮን ብር በመመደብ የዲዛይን ሥራው እየተሰራ የሚገኝ ሲሆን በቀጣይ በአእምሮ ጤና ላይ በሚሰሩ ሥራዎች አስተዳደሩ አስፈላጊውን እገዛ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑንና የአእምሮ ጤና የሁሉም ምህበረሰብ ክፍልና የባለድርሻ አካላት ርብርብ ሊሰሩበት የሚገባ በመሆኑ ሁሉም የኔ ጉዳይ ብሎ በጋራ ችግሩን ለመቅረፍ እንዲሰራ ጥሪያቸውን አቅርበዋል፡፡
የድሬዳዋ አስተዳደር ጤና ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ለምለም በዛብህም በአስተዳደራችን ለሱስ ተጋላጭ የሆኑ ማህበረሰቦች በርካቶች በመሆናቸው ለአእምሮ ጤና ችግር ውስጥም ያለው የማህበረሰብ ክፍልም ብዙ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በመሆኑም የችግሩ ስፋት የበርካቶችን ርብርብ የሚጠይቅ በመሆኑ ማህበረሰቡም ሆነ በአእምሮ ጤና ላይ የሚሰሩ ባለድርሻ አካላት ከመቼውም ይልቅ ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥተው መስራት እደሚገባቸው አስገንዝበው በዘርፉ እየሰሩ ያሉ አካላትንና በስፋት በአእምሮ ጤና ላይ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እያበረከቱ የሚገኙትን ፓድ ድሬዳዋ እንዲሁም ሚሺነሪ ኦፍ ቻሪቲን አመስግነዋል፡፡
በመድረኩ ከአማኑኤል ሆስፒታል በመጡት በዶ/ር ዮናስ ላቀውና በድል ጮራ ሪፈራል ሆስፒታል የአእምሮ ህክምና ክፍል ኃላፊ በሆኑት በዶ/ር ፂዎን ፅሁፎች የቀረቡ ሲሆን በአእምሮ ጤና ላይ ያተኮሩ ግጥምና አጭር ድራማም ለታዳሚዎች ቀርበዋል፡፡
ቀኑ በአገር አቀፍ ደረጃ ለ9ኛ ጊዜ ‹‹የአእምሮ ጤና ለሁሉም ፤ የበለጠ መዋዕለ ነዋይ ለብዙሃን ተደራሽነት!›› በሚል እና በድሬዳዋ አስተዳደር ደግሞ ‹‹ያለ አእምሮ ጤና ጤና የለም›› በሚል መሪ ቃል ነው ተከብሮ ነው የዋለው፡፡
ምንጭ : የድሬደዋ አስተዳደር ጤና ቢሮ


