9 ነጥብ 4 ቢሊየን ብር በሚደርስ የሙስና ወንጀል ላይ የምርመራ ስራ እያከናወነ መሆኑን የፌደራል ፖሊስ አስታወቀ::

    የተዘረፈ የህዝብ እና የመንግስት ሀብትን በማስመለስ 9 ነጥብ 4 ቢሊየን ብር በሚደርስ የሙስና ወንጀል ላይ የምርመራ ስራ እያከናወነ እንደሚገኝ የፌደራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቢሮ አስታወቀ።
    የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ጄነራል እና የወንጀል ምርመራ ቢሮ ኃላፊ ዘላለም መንግስቴ የ2013 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት አፈፃም ላይ መግለጫ ሰጥተዋል።
    በመግለጫቸውም በቅርቡ 9 ነጥብ 4 ቢሊየን ብር የሙስና ወንጀል ላይ ክስ ለመመስረት የኦዲት ሪፖርት እየተጠበቀ መሆኑን ገልፀዋል።
    የወንጀል ምርመራ ቢሮው በሩብ ዓመቱ በትምህርት ሚኒስቴር ላይ ባደረገው ምርመራ በ270 ሚሊየን ብር ዝርፊያ የተጠረጠሩ ግለሰቦች ላይ ምርመራ ተጠናቆ ክስ ተመስርቷል ብለዋል።
    ምክትል ኮሚሽነሩ በመግለጫቸው አክለውም፥ ከዚህ በኋላ በኢ መደበኛ አደረጃጀት የፖሊስን ስራ ተክቶ ለመስራት የሚደረግ እንቅስቃሴን መንግስት እንደማይታገስ ገልፀዋል።
    በኢ መደበኛ አደረጃጀት ሀሳባቸውን በሀይል ለመጫን የሚንቀሳቀሱ ቡድኖች ከድርጊታቸው ሊቆጠቡ ይገባል ሲሉም ተናግረዋል።
    ለአብነት በወላይታ ዞን ቁጥራቸው ከ4 ሺህ የሚበልጡ ከዚህ ቀደም በተለያየ የፀጥታ አካላት ውስጥ ሲሰሩ ቆይተው የተሰናበቱ የቀድሞ ሰራዊት አባላት በሚል ህገ ወጥ እንቅስቃሴ ሲያደርጉ መቆየታቸውን አንስተዋል።
    በዚህም በዞኑ ከሚነሳው በክልል የመደራጀት ጥያቄ ጋር ተያይዞ ህገ ወጥ በሆነ መንገድ ሃይል የማዘጋት እንቅስቃሴ መደረጉንም ነው የገለጹት፡፡
    ከዚህ ጋር በተያያዘ በዞኑ በተፈጠረው ችግር ተሳትፎ አላቸው ተብለው የተጠረጠሩ አካላት በቁጥጥር ስር ውለው ጉዳያቸው እየታየ ነው።
    በሌሎች አካባቢዎችም የወጣት አደረጃጀቶች ለእኩይ አላማ እየዋሉ በመሆናቸው ሊቆሙ ይገባል ተብሏል።
    ወንጀለኞችን ተጠያቂ በማድረጉ ሂደት ላይ አተኩሮ መስራቱን ገልጸው፥ በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን ከተፈጠረው ችግር ጋር ተያይዞ 504 ተጠርጣሪወች መያዛቸውን ጠቁመዋል።
    በተጠርጣሪዎች ላይ የሰውና የሰነድ ማስረጃ መቅረቡንም ነው ያነሱት።
    በሌላ በኩል ከአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያ ጋር ተያይዞ በተፈጠረ ግጭት በተጠረጠሩ 4 ሺህ 249 ግለሰቦች ላይ ምርመራ ተጠናቆ ክስ መመስረቱን አስረድተዋል።
    ከዚህ ውስጥ 3 ሺህ 377ቱ በፌደራል ደረጃ በ114 መዝገቦች ክስ የተመሰረተባቸው ናቸው።
    የህግ የበላይነትን ለማስከበር በሚሰራው ስራ በተለያዩ ወንጀሎች የተጠረጠሩ 1 ሺህ 105 ግለሰቦች እየተፈለጉ እንደሆነም ተገልጿል።
    ቢሮው በተጠርጣሪዎች አያያዝ ላይና ሰብዓዊ መብት አጠባበቅ ላይ ከፍተኛ ለውጥ ማምጣቱንም ነው የገለጸው።
    ምንጭ FBC