በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት የተቋረጠውን የመማር ማስተማሩን ስራ ለማስቀጠል በመንግስት፣ በትምህርት ሚኒስቴር እና በጤና ሚኒስቴር የተቀመጡ የኮቪድ-19 መከላከል መሥፈርቶችን በማሟላት ሁሉም ትምህርት ቤቶች መደበኛ የመማር ማስተማር ለመጀመር ዝግጅታቸውን መጠናቀቃቸውን የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር የትምህርት ቢሮ አስታውቋል፡፡
የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር የትምህርት ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ሙሉካ መሐመድ ለዋልታ ቴሌቪዥን እንደገለጹት በድሬዳዋ አስተዳደር የትምህርት ስራውን ለማስጀመር ከባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር ለመማር ማስተማሩ የሚያግዙ ግብዓቶችን የማሟላት የተሰባበሩ ወንበሮችን የመጠገን፣ ትምህርት ቤቶችን በማደስና ተጨማሪ የማስተማሪያ ክፍሎችን ለማመቻቸት ባለድርሻ አካላት ከአስተዳደሩ ጋር ተባብረው ሰርተዋል።
የከተማ አስተዳደሩ ተማሪዎች ከኮሮናቫይረስ ራሳቸውን በመጠበቅ የተቋረጠውን የትምህርት ሥራ በማካት የተሻለ ውጤት አስመዝግበው የትምህርት ጥራት ማረጋገጥ እንዲቻል ሁሉም የበኩሉን ድርሻ ሊወጣ ይገባል ብሏል።
ለዋልታ አስተያየታቸውን የሰጡት የሳቢያን ቁጥር ሁለት ርዕሰ መምህር ወንድወሰን ንጉሴ ትምህርት ቤቱ ተማሪዎችን ለመቀበል ቅድመ ዝግጅት ያጠቀቀ ሲሆን ሁሉም ካልተደጋገፈ በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ወቅት ከባድ በመሆኑ የመማር ማስተማሩን ስራ በተገቢው እንዲያከናውኑ ሁሉም ዜጋ ትምህርት ቤቱን በመደገፍ የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል።
ርዕስ መምህሩ አክለውም የማስተማር ስራውን በሶስት ፈረቃ ለማድረግ ከባለድርሻዎች ጋር ምክክር እየተደረገ መሆኑን ገልፀው፣ በዚህ ከባድ የወረርሽኝ ጊዜ ሁሉም ሊተባበር ይገባል ብለዋል።
በቀጣይ ሣምንት በገጠር ቀበሌዎች ትምህርት ቤቶች የሚከፈት ሲሆን ከጥቅምት ወር አጋማሽ ጀምሮ ደግሞ በከተማ ቀበሌ ውስጥ ያሉት ትምህርት ቤቶች የመማር ማስተማሩን እንደሚጀምሩ አቶ ወንድወሰን ገልፀዋል።
ምንጭ ፡ ዋልታ


