የአስተዳደሩ ገቢዎች ባለስልጣን በሲግታክስ (Standard Integrated Government Tax Administration system) ቴክኖሎጂ የማስጀመሪያ እና የምስጋና ስነ ስርዓት የአስተዳደሩ ከፍተኛ አመራሮች እና የባለስልጣኑ ፈፃሚ እንዲሁም ባለሙያዎች በተገኙበት ተካሂዷል፡፡
የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ አሀመድ መሀመድ ቡህ በስነ ስርአቱ ላይ እንደተናገሩት የታክስ አሰባበሰብ ስርዓቱ ዘመኑ የደረሰበትን ቴክኖሎጂ ተጠቅሞ በመስራት በአግባቡ ግብርን ለመሰብሰብና ቀጣይነት ያለውን ልማት የሚናፍቅ ድህነትን የሚጠየፍ ህዝብ እና ጠንካራ ሀገር እንዲኖረን ጠንካራ የታክስ አስተዳደር ስርዓት ሊኖር ይገባል ብለዋል፡፡
ከንቲባ አህመድ መሀመድ ቡህ ለተቋሙ ሰራተኞች ባስተላለፉት መልዕክት በተያዘው በጀት ዓመት በአስተዳደሩ 1.7 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ለመሰብሰብ በመታቀዱ የባለስልጣን መስሪያ ቤቱ አስፈጻሚ አካል አሁን ካለው ተነሳሽነት በተሻለ ኃላፊነታቸውን በአግባቡ እንዲወጡ በማስገንዘብ አስተዳደሩ ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የጀመረውን የሪፎርም ስራ ውጤታማ እንዲሆን ተገቢውን ሁሉ ድጋፍ እንደሚያደርጉ ገልፃዋል፡፡
የአስተዳደሩ ገቢዎች ባለስልጣን ኃላፊ አቶ አብዱሰላም መሀመድ በስነ ስርዓቱ ላይ እንደተናገሩት የተጠናከረ እና የዘመነ መረጃ ስርዓት መኖር በታክስ አስተዳደር ስርዓት ውስጥ የህግ ተገዢነት እንዲሰፋ እና ለግብር አወሳሰንና አሰባበሰብ ስርዓት ግንባታ ዓይነተኛ መሳሪያ ነው ብለዋል፡፡
ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ቀደም ሲል ይጠቀምበት የነበረውን የአስተዳደሩ ሎጎ በራሱ የሆነ ሎጎ መቀየሩንም አስተዋውቋል፡፡
በትዕግስት ቶሎሳ


