በድሬዳዋ አስተዳደር የኢንዱስትሪ ፓርክ በትላንትና እለት መርቀው የከፈቱት የኢ.ፌ.ድ.ሪ ጠ/ሚ ዶ/ር አብይ አህመድ ባደረጉት ንግግር ፓርኩ የአካባቢው ነዋሪ የሆኑ ወጣቶች አዳዲስ ክህሎቶችን እና እውቀትን እንዲገበዩ እና የመስራት አቅማቸውን በተግባር እንዲገልጡ እንደሚያስችል ገልፀዋል፡፡
ፓርኩ በአጭር ጊዜ ውስጥ የሰራቸው የመኖሪያ ቤቶች፣ የእግረኛ መንገዶች እና የአረንጓዴ አሻራ በግቢ ውስጥ መኖሩ በሌሎች አካባቢዎች ከተገነቡት ፓርኮች ለየት ያደርገዋል ሲሉ ጠ/ሚ ዶ/ር አብይ አህመድ ተናግረዋል፡፡
በሀገሪቱ የተገነቡት የኢንዱስትሪ ፓርኮች ለድሬደዋ ጎረቤት ሀገር ጅቡቲ በቅርበት መሆኑ ጠቀሜታው የጎላ እንዲሚያደርገው ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብ አህመድ አስታውቀዋል፡፡
የሀገሪቱን እና የድሬደዋ ሁለንተናዊ የብልፅግና ጉዞ ስኬታማ እንዲሆን ፣ መሰል ፓርኮች እንዲሰፍር እና ድሬደዋ የልማት፣ እንደስሟ የፍቅር ስፍራ እንድትሆን በመደመር እሳቤ ሁሉም የተጣለበትን ኃላፊነት እንዲወጣ አሳስበዋል፡፡
የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ አቶ አህመድ መሐመድ ቡህ በምረቃ ስነ-ስርዓቱ ላይ ባደረጉት ንግግር እንደተናገሩት ለአስተዳደሩ የተገነባው የኢንዱስትሪ ፓርክ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያለው ፓርክ በመሆኑ በኢኮኖሚ፣ ማህበራዊ መስኮች ለውጥ ለማምጣትና የመልካም አስተዳደር ችግሮች እንዲቀረፍ የራሱ የሆነ ሚና አለው ብለዋል፡፡
የአስተዳደሩ ከንቲባ አቶ አህመድ አህመድ ከዚህ ጋር በማያያዝ የፓርኩ ተመርቆ አገልግሎት መጀመር ድሬደዋ የምስራቅ የኢንዱስትሪ ከተማ የማድረግ ራዕይ ለማሳካት እና ስራ አጥነትን ትርጉም ባለው መንገድ ለመቀነስ ያስችላል ብለዋል፡፡
የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ሳንዶካን ደበበ ባደረጉት ንግግር የድሬዳዋ ኢንዱስትሪ ፓርክ የተገነባው ከፍተኛ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ባለበት በመሆኑ የነበረውን የኢኮኖሚ ኮሪደርነት ለመመለስ ከሌሎች ግዙፍ ፕሮጀክቶች ጋር በመሆን ፓርኩ የራሱን ጉልህ አስተዋጽኦ ያደርጋል ብለዋል፡፡


