የህወሃት አጥፊ ቡድን በቀርቡ በሰሜን እዝ ላይ ድንገተኛ ጥቃት መፈፀሙን ተከትሎ የሀገር መከላከያ ሠራዊታችን እርምጃ መውሰድ መጀመሩንና የህግ የበላይነት የማስከበር ስራ እየሰራ መሆኑን ተከትሎ ዜጎች መንግስት እየወሰደ ያለውን እርምጃ በመደገፍ ከመንግስት ጎን መሆናቸውን እየገለፁ ይገኛሉ፡፡
በድሬዳዋ እስተዳደር ስር ከሚገኙ ገጠር ቀበሌዎች አንዷ በሆነችው ለገቢራ ገጠር ቀበሌ ነዋሪዎች በወቅታዊ የሀገራችን ሁኔታ ላይ ውይይት ያደረጉ ሲሆን በውይይታቸውም የኢፌድሪ መከላከያ ሠራዊት በህወሃት አጥፊ ቡድን ላይ እየወሰደ ያለውን እርምጃ እንደሚደግፉና በማንኛውም ጊዜ ቢሆን መንግስት የሚያደርገውን ሀገራዊ ጥሪ በመቀበል እስከ ህይወት መስዋዕት ለመክፈል ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
አጥፊው ቡድን ሀገርን ለማፍረስ ሚያደርገውን የሽብር ተግባር አንታገሰውም ያሉት የቀበሌው ነዋሪዎች በተለይም ቡድኑ እኩይ አላማውን ለማስፈፀም በየአካባቢው ያሰማራቸውን የጥፋት ሀይሎች በንቃት በመከታተል አካባቢያችንን በመጠበቅ የበኩላችንን እንወጣለን ብለዋል፡፡ የቀበሌው ነዋሪዎች አክለውም የውስጥ ችግሮቻችንን ለጊዜው በማቆየት ቅድሚያ ሀገርን ከጥፋት ለመታደግ ሁላችንም ልንረባረብ ይገባልም ብለዋል፡፡
የቀበሌው ሴቶች በበኩላቸው በዚህ የስጋት ጊዜ ወንዶች በእርሻ ስራ ላይ በሚሆኑበት ጊዜ እንኳን ቢሆን አዳዳዲስ ፀጉረ ልውጥ የሆኑ ግለሰቦችን በንቃት በመከታተል ለቀበሌው የፀትታ አካላት ጥቆማ እንሰጣለን ብለዋል፡፡
ተመሳሳይ ውይይት በሁሉም የአስተዳደሩ ቀጠር ቀበሌዎች የተካሄደ ሲሆን መላው የድሬዳዋ ገጠር ነዋሪዎች በህወሃት አጥፊ ቡድን ላይ ተመሳሳይ አቋም እንዳላቸው ነው መረዳት የቻልነው፡፡


