መላው ህዝብ ለሀገር መከላከያ ሠራዊት እየሰጠ ያለው ድጋፍና ክብር የህግ የበላይነት ለማረጋገጥ እየተካሄደ ያለው ዘመቻ በፍጥነትና በስኬት እንዲጠናቀቅ አቅም የሚፈጥር መሆኑን የኢፌደሪ አየር ኃይል የምስራቅ ምድብ ዋና አዛዥ ኮሎኔል አበበ ለገሰ አስታወቁ፡፡
በድሬዳዋ አስተዳደር የጀልዴሳ ገጠር ክላስተር ነዋሪ አርብቶ አደሮች ለሀገር መከላከያ ሠራዊት 430 ሺህ ብር የሚያወጡ ስምንት ግመሎችና አንድ ሰንጋ ትናንት በድጋፍ አበርክተዋል።
ድጋፉን የተረከቡት ኮሎኔል አበበ በወቅቱ እንደገለጹት፤ የህወሀት የጥፋት ቡድን በሰሜን እዝ መከላከያ ሰራዊት ላይ የፈጸመውን ጥቃት ተከትሎ ህዝቡ ድርጊቱን በማውገዝ ለመከላከያ ሰራዊት ያለውን ድጋፍ፣ ፍቅርና ክብር እየገለጸ ነው።
ህዝቡ የሰራዊቱን የህግ ማስከበር ዘመቻ በሞራል፣ በገንዘብ፣ በቁሳቁስ፣ በሙያ፣ በደም ልገሳና በሌሎች ድጋፍ አጋርነቱን እያሳየ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ይህ ደግሞ ህግ የማስከበር ዘመቻው በአጭር ጊዜ በስኬት እንዲጠናቀቅ አቅም የሚፈጥር መሆኑን ተናግረው፤ ህዝቡ ላሳየው ክብርና ድጋፍ በሰራዊቱ ስም አመስግነዋል።
የምስራቅ ዕዝ ደረጃ 3 ሆስፒታል አዛዥ ተወካይ ሌተናል ኮሎኔል ብርሃኑ ዘውዴ በበኩላቸው “መላው የሀገሪቱ ዜጎች ለሠራዊቱ ያሳዩት ክብርና እየለገሱ ያለው ድጋፍ ሠራዊቱ ሀገራዊ ተልዕኮውን ይበልጥ ለማጠናከር ያግዘዋል” ብለዋል።
ለሠራዊቱ የተሰጠው ክብር ከኃላው ግዙፍ ደጀን መኖሩ የታየበት እንደሆነ ገልጸዋል።
የድሬዳዋ አስተዳደር ነዋሪዎች እያደረጉ ላለው ድጋፍም አመስግነዋል፡፡
“የጀልዴሳ አርብቶ አደር እንደ ልጆቹ የሚወዳቸውን ግመሎች በድጋፍ መስጠቱ ለሠራዊቱ ያለውን ታላቅ ፍቅር ያመለክታል” ሲሉም ምስጋና አቅርበዋል፡፡
ምክትል አስር አለቃ ነገራ ታመነ ለሠራዊቱ እየተሰጠ ያለው ክብር የትኛውንም ተልዕኮ በታላቅ ጀብዱ ለመፈፀም የሚያነቃቃና ሞራል እንደሚሰጥ ገልጸዋል፡፡
የጀልዴሳ ገጠር ክላስተር አርብቶ አደሮችም ለሠራዊቱ የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ በተወካያቸው አርብቶ አደር ቱጋሌ ዑመር አብዲ በኩል አረጋግጠዋል።
ሠራዊቱ ሰላም ለማስፈንና ወንጀለኞችን ለህግ ለማቅረብ ለጀመረው ዘመቻ መሳካት የህይወት መስዋዕትነትን ጨምሮ አስፈላጊውን ሁሉ እንደሚያደርጉ ተናግረዋል፡፡
በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የድሬዳዋ አስተዳደር የንግድ፣ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኃላፊ አቶ ከድር ጁሃርና የድሬዳዋ ብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ መብራቴ ገብረየስ ለተደረገው ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል፡፡


