በመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ የመረጃ አካላትን ማብቃትና ማፍራት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ሚካኤል እንዳለ ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር ሚኒሚዲያዎች ለትምህርት ቤቶች ማህበረሰብ ቅርብ በመሆን መረጃን ተደራሽ በማድረግ ረገድ አይነተኛ አስተዋጽኦ አላቸው ብለዋል፡፡
ይህ አሁን የተዘጋጀው ስልጠና በሚኒሚዲያ አዘገጃጀትና ኮሮና ቫይረስን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በወጣው የትግበራ መመሪያ ዙሪያ የሚኒሚዲያ ተጠሪዎች ግንዛቤ እንዲጨብጡ መሆኑን አቶ ሚካኤል ገልፀዋል፡፡
የሚኒሚዲያዎችን አቅም ለመገንባት የሚሰጡ ስልጠናዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የገለፁት አቶ ሚካኤል ሚኒሚዲያዎች በተለይም የሰላምን ዋጋ በመገንዘብ ለትምህርት ቤቱ ማህበረሰብ ስለ ሰላም ሳይሰለቹ መልዕክት እንዲያስተላልፉ አሳስበዋል፡፡
ከአንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ለተውጣጡ የሚኒሚዲያ ተጠሪዎች የተሰጠው ስልጠና የሚኒሚዲያ ፅንሰሃሳብና አተገባበር ላይ ያተኮረ ነበር፡፡የሀገራዊ ገፅታ ግንባታና የውጭ ግንኙነት ቡድን መሪ በሆኑት በአቶ ሄኖክ ይልማ በተሰጠው ስልጠና የሚኒሚዲያ ምንነት፣የሚኒሚዲያ አስፈላጊነት፣በትምህርት ቤት ውስጥ ሚኒሚዲያን ለመመስረት የሚያስፈልጉ ቁልፍ ጉዳዮች የተዳሰሱ ሲሆን የሚኒሚዲያ አጠቃቀምና አያያዝን ጨምሮ ከሚኒሚዲያ ጋር የተያያዙ ዋናዋና ርዕሰጉዳዮች በስልጠናው ተቃኝተዋል፡፡
ሚኒሚዲያዎች ለሰላም ዕሴት ግንባታ ባላቸው ሚና ላይም ገለፃ ተደርጓል፡፡
ሚኒሚዲያዎች ተማሪዎች የመከባበር፣የመዋደድ፣የጋራ ዕሴቶቻቸውን የመጋራት፣በአንድነት ውስጥ ያለውን ልዩነት አምኖ የመቀበል ዕሴቶችን እንዲገነዘቡ ትልቅ አስተዋፅኦ እንዳላቸው በስልጠናው ተገልጿል፡፡
ኮቪድ 19ን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በወጣው የትግበራ መመሪያ ዙሪያ ከጤና ቢሮ በመጡት አቶ ታሪኩ አበበ በተሰጠው ስልጠና ሰፊ ገለፃ ተደርጓል፡፡
የትምህርት ቤቱ ማህበረሰብ ኮቪድ 19ን ለመከላከል መወጣት ስለሚገባው ሃላፊነት ተዳሷል፡፡ ኮቪድ 19 አሁንም ያለ በመሆኑ መምህራንና ተማሪዎች በመቀናጀት እንዲሁም መዘናጋትን በማስወገድ ከወረርሽኙ እራሳቸውን፣ቤተሰባቸውንና ማህበረሰቡን እንዲጠብቁ መልዕክት ተላልፏል፡፡


