ወጣቱ ከአደንዣዥ እፅና ከመጤ ልማዶች በመላቀቅ ሃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጥሪ ቀረበ::

    የድሬደዋ አስተዳደር የወጣቶች እና ስፖርት ኮሚሽን ወጣቶችን ማፍራትና ማብቃት ዳይሬክቶሬት በገጠርና በከተማ ቀበሌ ለተውጣጡ ወጣቶችና ወላጆች እንዲሁም ለሀገር ሽማግሌዋችና የሀይማኖት አባቶች በአደንዣዥ እፅ እና መጤ ልማዶች ዙሪያ ግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና በድሬደዋ ዪኒቨርስቲ የስነ ልቦና ባለሙያዋች እየተሰጠ ነው።
    አራተኛ ቀኑን ያስቆጠረው የግንዛቤ ማስጨበጫ በዛሬው እለት ከቢያዋሌና ከዋሂል ክላስተር ለመጡ ሰልጣኞች ንግግር ያደረጉት ያስተዳደሩ ወጣቶችና ሰፖርት ኮሚሽን ወጣቶችን ማፍራትና ማብቃት ዳይሬክቶሬት አቶ እስክንድር አህመድ እንደተናገሩት ወጣቱን በኢኮኖሚ፣ማህበራዊና ፖለቲካዊ ዘርፍ ያላቸውን ተጠቃሚነት በከተማው ያለውን የተሻለ እንቅስቃሴ ወደ ገጠሩ ለማስፋት ታስቦ የግንዛቤ ማስጨበጫው መዘጋጀቱን ገልፀዋል።
    አቶ እስክንድር ከዚህም ጋር በማያያዝ ወጣቱ ከአደንዣዥ እፅና ከመጤ ልማዶች እራሳቸውን በማራቅ እራሳቸውን እና ሀገራቸውን በመጥቀም የድርሻቸውን እንዲወጡ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
    በሰሜኑ የሀገር መከላከያ ሰራዊት በጁንታው ቡድን የደረሰውን ጉዳት ተከትሎ የአስተዳደሩ ወጣቶች ደሜን ለጀግናዬ በሚል መሪ ቃል ደም በመለገስ ያደረጉትን ድጋፍ በማመስገን በቀጣይም እያደረጉት ያለውን ድጋፍ በማጠናከር ከፀጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት አካባቢያቸውን እንዲጠብቁ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።
    የድሬደዋ አስተዳደር የወጣቶች እና ስፖርት ኮሚሽን ወጣቶችን ማፍራትና ማብቃት ዳይሬክቶሬት የወጣትን ማብቃት ቡድን መሪ አቶ መስፍን አየለ በሰጡት አስተያየትም ወጣቱ ከአደንዣዥ እፀና ከመጤ ልማዶች በመራቅ በስራ እድል ፈጠራና በስራ ላይ ከማብቃት አንፃር ስልጠናው መዘጋጀቱ የጎላ ሚና አለው ብለዋል።
    በስልጠናው የተሳተፉ ተሳታፊዋችም ስልጠናው ቀጣይነት ያለው ቢሆን የበለጠ ለውጥ እንደሚያመጣ በመጠቆም እራሳችንን ለመመልከት ያስቻለ ስልጠና ነው ብለዋል።