የአደንዛዥ እጽ እና መጤ ጎጂ ባህሎች በወጣቱ ላይ እያስተከሉ ያለውን ቀውስ ለማስወገድ ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን እንዲወጡ ጥሪ ቀርቧል

    የድሬዳዋ አስተዳደር የወጣቶችና ስፖርት ኮሚሽን በአስተዳደሩም ሆነ በአገር አቀፍ ደረጃ የአደንዛዥ እጽ እና መጤ ጎጂ ባህሎች በህብረተሰቡ ላይ እያስከተሉ ያሉትን ማህበራዊ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ቀውሶች ለመከላከል ሁሉን አቀፍ የሆነ ዘመቻ ተግባራዊ ማድረግ ጀምሯል፡፡
    በኮሚሽኑ የወጣቶች ማብቃት ቡድን መሪ አቶ መስፍን አየለ ሁሉም የህብረተሰቡ ክፍሎች መጤ ጎጂ ልማዳዊ ባህሎች እና የአደንዛዥ እጽ በህብረተሰቡ ላይ እያስከተሉ ያሉትን ችግሮች ለመከላከል እንዲያነሱ ጠይቀዋል፡፡
    ወጣቱን በተሰማሩበት መስክ ስኬታማ እዲሆኑ ለማስቻል ከስፖርት ኮሚሽን በተጨማሪ ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን እንዲወጡ ለማስቻል ታስቦ ስልጠናው መዘጋጀቱንም አቶ መስፍን ተናግረዋል፡፡
    በአስተዳደሩ ዘጠኙንም የከተማ ቀበሌ እና የገጠር ክላስተሮችን ያማከለ የግንዛቤ ማስጨበጥ እና የንቅናቄ መድረክ ስራ እየተሰራ ይገኛል፡፡
    በዚህ መድረክ ወጣቶች በአደንዛዥ እጽ በመጠመድ ለአገር ማበርከት ያለባቸውን ሚና ማበርከት ሳይችሉ ከመቅረታቸው በተጨማሪ ለአገር ሰላምና ፀጥታ ችግር እየፈጠረ መምጣቱን ኮሚሽኑ ከፍተኛ ባለሞያ የሆኑት አቶ አመዲን አሊይ አህመድ ተናግረዋል፡፡ በዚህም ህብረተሰቡን በንቃት በማሳተፍ እና ለተጀመረው ለውጥ ቀጣይነት እነዚህን ሁለትዮሽ ችግሮች መዋጋት በማስፈለጉ ስልጠናው መዘጋጀቱ ታውቋል፡፡