6 ሺህ ለሚሆኑ ሰዎች የኮቪድ 19 ክትባትን መከተብ የሚያስችል ክትባት ወደ ድሬዳዋ አስተዳደር መግባቱ ይታወቃል ። በዛሬው እለትም የመጀመሪያው ዙር የኮቪድ 19 ክትባት በሳቢያን የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል መሰጠት ተጀምሯል።
በክትባት ማስጀመሪያ መርሀ-ግብሩ ላይ በመገኘት ንግግር ያደረጉት የድሬዳዋ አስተዳደር ምክትል ከንቲባና የንግድ ኢንደስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ሀላፊ የሆኑት አቶ ከድር ጁሀር የኮሮና ቫይረስ ወረርሺኝ በሽታ በአስተዳደሩ ላይ በተከሰተበት ወቅት የጤና ባለሞያዎች ህይወታቸውን ሳይሰስቱ የወገናቸውን ህይወት ለመታደግ ለከፈሉት መስዋት ምስጋናቸውን አቅርበው ነዋሪው ህብረተሰብም ከጤና ባለሞያዎች ጎን በመቆም ሊተባበር እንደሚገባም አቶ ከድር ጁሀር ተናግረዋል።
የኮቪድ 19 ክትባትን በግልም ሆነ በመንግስት ሆስፒታልና ጤና ጣቢያዎች ላይ ለሚሰሩ የጤና ባለሞያዎች በሙሉ እንደሚከተቡና በቀጣይም ደግሞ ክትባቱ ወደ ሀገራችን የሚገባውን መጠን ከግምት ውስጥ በማስገባት እድሜያቸው ለገፋና ተጋላጭ ለሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች እንደሚሰጥ የድሬዳዋ አስተዳደር ጤና ቢሮ ሀላፊ የሆኑት ወ\ሮ ለምለም በዛብህ ተናግረዋል ።
በተለይም ለኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በሽታ ተጋላጭ ሊሆኑ የሚችሉት የጤና ባለሞያዎች እንደመሆናቸው መጠን ይሄንን ክትባት መከተባቸው እራሳቸውን ከበሽታው እየተከላከሉ ህብረተሰቡንም ለማገልገል እንደሚያስችልና ክትባቱንም በመከተባቸው መደሰታቸውን የጤና ባለሞያዎች ተናግረው ህብረተሰቡም እራሱን ከኮሮና ቫይረስ በመጠበቅ ሌሎች ወገኖቹን ማዳን እንዳለበት የጤና ባለሞያዎቹ ተናግረዋል ።
በመርሀ-ግብር ላይም ከፍተኛ የመንግስት አመራሮችና የጤና ባለሞያዎች እንዲሁም የሀይማኖት አባቶች ተገኝተዋል ።


