12ኛው ዙር #የብስክሌተኞችና #የእግረኞች የአመቱ ማጠናቀቂያ መርሀግብር ድሬደዋ ላይ በተለያዩ ዝግጅቶች በድምቀት ተከብሯል፡፡

    በስነስረአቱ ማህበረሰቡም ሆነ ባለድርሻ አካላት ለትራፊክ አደጋ መከላከል ስራው ድጋፋቸው እንዲጠናከር ጥሪ ቀርቧል፡፡
    በስነ ስረአቱ ላይ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት በትራንስፖርት ባለስልጣን ድሬደዋ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ሰአዳ አዋሌ እንደተናገሩት ማህበረሰቡ አማራጭ የሞተር አልባ ተሽከርካሪዎችንና የእግር ጉዞ ባህልን እንዲያጎለብት ገንዛቤን በመፍጠር እየደረሰ ያለውን የትራፊክ አደጋ ለመቀነስ ታስቦ መርሀግብሩ በትራንስፖርት ሚኒስትር እና በትራንስፖርት ባለስልጣን ድሬደዋ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ትብብር ወር በገባ የመጨረሻው እሁድ በማካሄድ 12ኛ ዙር ላይ ደርሷል ብለዋል፡፡
    በዋናነት በአመቱ በተካሄዱ የግንዛቤ መፍጠሪያ ስራዎች ማህበረሰቡ የሞተር አልባ ተሽከርካሪንና የእግር ጉዞ ባህልን እንዲያዳብር ግንዛቤ መፍጠር ተችሏልም ብለዋል፡፡
    ዋና ዳይሬክተሯ አያይዘውም አሁን ላይ በተለይ ከትራፊክ አደጋ መጨመር ጋር ተያይዞ እንደሚኒስቴር መስሪያቤትና ቅርንጫፍ ጽ/ቤቱ ከሚሰረራው የማስገንዘብ ስራ በተጓዳኝ የማህበረሰቡና የባለድርሻ አካላት ተሳትፎ ባዲሱ አመት ከምንጊዜውም በላይ እንዲጨምር ጥሪ ያቀረቡ ሰሆን በተለይ አሽከርካሪዎች ከፍጥነት በላይ ባለማሽከርከር ሀላፊነታቸውን እንዲወጡም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
    ከምንግዜውም በላይ ስርጭቱ እየጨመረ የመጣው የኮሮና ወረርሽኝ ሌላ ስጋት ሌላ ፈተና ሀኗል ያሉ ሲሆን በተለይ ማህበረሰቡ ትራንስፖርትን ሲጠቀምም ሆነ አሽከርካሪው ሲያሽከረክር ማስክን ባግባቡ በመጠቀም ራሱን ከቫይረሱ እንዲታደግ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
    ትራንስፖርት ባለስልጣን ድሬደዋ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት የመንገድ ትራፊክ ደህንነት ማሻሻያ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ምክትል ኮማንደር ጉልማ ታዬ በበኩላቸው በመድረኩ ላይ ማህበረሰቡ በትራፊክ አደጋ እንዳይጎዳ ህግን አክብሮ መንገዱን ባግባቡ እንዲጠቀምና የሞተር አልባ ተሽከርካሪንና የእግር ጉዞን ባህል እንዲያደርግ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
    በስተመጨረሻም የአካል ብቃት እንቅስቃሴዎችን በማድረግና በተመረጡ ጎዳናዎች ላይ የሳይክልና እግር ጉዞ በማካሄድ መርሀግብሩ ተጠናቋል፡፡
    በዘውገ አውላቸው