በአለም አቀፍ ለ 6 ተኛ በአስተዳደራችን ደግሞ ለ 4 ተኛ ጊዜ ” የማወቅ መብት በመረጃ ተደራሽነት በተሻለ መልሶ ግንባታ ” በሚል መሪ ቃል የሚከበረውን አለም አቀፍ የመረጃ ተደራሽነት ቀንን አስመልክቶ በድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ የፓናል ውይይት ተካሂዷል ።
ወቅታዊና ትክክለኛ መረጃን ተደራሽ ማድረግ ሰላምን ለማስፈን ብሎም የኮሮና ቫይረስ ወረርሺኝ በሽታን ለመከላከል ያለውን ቁልፍ ሚና ሁላችንም የምንገነዘበው መሆኑን የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት የሆኑት ዶክተር ኡባህ አደም ተናግረው የዘድሮውም የአለም አቀፍ የመረጃ ተደራሽነት ቀን መሪ ቃልም በተለይም በችግር ጊዜ የመረጃ ተደራሽነት ያለውን ልዩ ዋጋ መሰረት ያደረገው ለዚህ መሆኑን ዶክተር ኡባህ በመድረኩ ላይ ተናግረዋል ።
ዛሬ ላይ ወቅታዊና ትክክለኛ መረጃ የማግኘት ጉዳይ አዳጋች እንደሆነና ነገር ግን ወቅታዊና ትክክልኛ መረጃን ተደራሽ ማድረግ ሀገርን ለመገንባት ያለውን ቁልፍ ሚና ሁሉም ሰው የሚገነዘበው መሆኑን የህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም ድሬዳዋ ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት ሀላፊ የሆኑት አቶ አሽኔ አየለ ተናግረው የፓናል ውይይቱንም ለማዘጋጀት የህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም ፣ የድሬዳዋ አስተዳደር ጤና ቢሮ እንዲሁም የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ላደረገው አስተዋፆ አቶ አሽኔ ምስጋናቸውን አቅርበዋል ።
በፕሮግራሙ ላይም የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ መምህርንና ሰራተኞች ፣ የመንግስት አስፈፃሚ አካላትና ባለድርሻ አካላት ተሳታፊ ሆነዋል ።


