የተከበራችሁና የተወደዳችሁ ለዛሬ የመንግስት ምስረታ በነፃ ፍቃዳችሁ ይሁንታችሁን የሰጣችሁ የድሬዳዋ አስተዳደር መላው ነዋሪዎች
ክብራትና ክቡራን:-
በቅድሚያ የሉዓላዊነት መገለጫ በሆነው በተከበረው የአስተዳደሩ ምክር ቤት ፊት በመገኘቴ እንዲሁም እትብቴ በተቀበረባት፣ በተማርኩባትና፣ በተለያዩ የስራ ሃላፊነቶች ባገለገልኩባት የትውልድ ከተማዬ ትልቅ ሃላፊነትና አደራን በመቀበል፣ ድሬዳዋችንን እንድመራ በከንቲባነት በመሰየሜ የተሰማኝን ታላቅ ክብር እና ደስታ ስገልጽ ከልብ በመነጨ ምስጋና ነው፡፡
በሀገራችን ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ በሚባል ደረጃ ነፃ፣ ፍትሃዊ እንዲሁም ህዝብ በነቂስ የተሳተፈበት ምርጫ አካሂደን ለዛሬ የመንግስት ምስረታ በመብቃታችን የተሰማኝን ልባዊ ደስታና ኩራት ለመግለፅ እወዳለሁ፡፡
የድሬዳዋ አስተዳደር ነዋሪዎች መንግስት ይመሰረት ዘንድ ዛሬ እዚህ የተሰየምን እኔ እና መላው የምክር ቤት አባላት እንድናገለግላችሁ ስለመረጣችሁን በራሴና በአዲሱ አስተዳደር ስም ምስጋናዬን እገልጻለሁ፡፡
በዋናነት ከአዲሱ አስተዳደር የሚጠበቀው የድሬዳዋ ነዋሪዎቻችንን ህይወት ትርጉም ባለው መልኩ ለማሻሻል እና የተሻለና ጠንካራ አስተዳደር በመፍጠር ብልጽግናን ለማምጣት መሆኑን በሚገባ እንገነዘባለን፡፡
ይህንን ለማድረግም እዚህ ከምትገኙ የተከበራችሁ የምክር ቤት አባላት፣ ዛሬ አዲስ ካደራጀሁት የአስተዳደሩ አስፈጻሚዎች እና ከመላው ነዋሪዎች ጋር በድሬዳዋዊ ፍቅር፣ መተጋገዝ እና የአንድነት መንፈስ ለመስራት ከአሁኑ ጉጉና ዝግጁ መሆኔን ስገልጽ ባለፉት ጊዜያትን እንደትምህርት ወስደን ነው፡፡
በተለይም በአስተዳደራችን ባለፉት ሶስትና አራት አመታት በሀገራችን የመጣው እምርታዊ ለውጥ በድሬዳዋችን መሰረት እንዳይዝና ነዋሪዎችን የለውጡ ቱሩፋት ከሆኑት የዴሞክራሲ የፍትህና የኢኮኖሚ ነፃነት ተጠቃሚነት ተቋዳሽ እንዳይሆኑ ያልተፈነቀለ ድንጋይ አልነበረም፡፡
ከዚህም መካከል ድሬዳዋዊ ከሆነው እና በመላው ሀገሪቱ የምንታወቅበትን የጋራና ጠንካራ የስነ-ልቦና ማህበረሰባዊ ስሪት ለማደብዘዝ የተዘራብንን የልዩነት የዘር አረም በድሬዳዋዊ የፍቅርና ተደጋግፎ የመኖር ባህላችን መንጥረን ባለፈው አንድ አመት ተኩል ሠላማችንን በራሳችን ጥረት መመለስ መቻላችን የቅርብ ጊዜ ትውስታችን ነው::
የውስጥ አንድነታችንን በማስጠበቃችን በአለም የተከሰተውን የኮቪድ19 ወረርሽኝን በአስተዳደራችን ተቋቁመን፤ እርስ በእርሳችን ተደጋግፈን በሀገራዊ ጉዳይ በጋራ ተሰልፈን፤ 6ኛውን አገራዊና አስተዳደራዊ ምርጫ የሚበጀንን መርጠን ዛሬ ለመንግስት ምስረታ በቅተናል::
በቀጣይ 5 አመት ድሬዳዋችን ከነዋሪዎቿ አልፋና ተርፋ የምስራቁ የሀገራችን የኢንዱስትሪ፣ የንግድና የኢኮኖሚ ማዕከል እንድትሆን ለተለምነው የብልፅግና እቅድ ወሳኝ አቅም ስለሆነ ሁላችንም እንድንረባረብ ጥርዬን አቀርባለሁ፡፡
ድሬዳዋችን ኢትዮጵያዊት የፍቅርና ብልፅግና ተምሳሌት ለማድረግ የአስርና የአምስት አመት ስትራቴጂክ እቅድ ያዘጋጀን ሲሆን ነሪዎቻችን ዘር፣ ሃይማኖት፣ እድሜ፣ አካል ጉዳተኝነት፣ ፆታ፣ ኑሮ ደረጃና ቦታ ሳይገድባቸው በኢኮኖሚ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮችን ላይ ያለምንም ተዕፅኖ በእኩል ተሳታፊና ተጠቃሚ ማድረግን አላማ አድርጎ አስተዳደሩ አዘጋጅቷል፡፡
በከተማ የኑሮ ውድነትና ስራ አጥነት በገጠር የምግብ ዋስትና የማረጋገጥ ፈተና የሚስተዋልብን እንደመሆኑና ችግሩም የእያንዳንዳችንን ቤት እያንኳኳ ያለ እና ነዋሪዎቻችን ስጋት ላይ የከተተ መሆኑን እንረዳለን፡፡
በመሆኑም እዚህ በተከበረው ምክር ቤት ለምትገኙ ክቡራን የህዝብ እንደራሴዎች ብቻ ሳይሆን ለመላው የአስተዳደራችን ነዋሪዎች ላረጋገጥላችሁ የምወደው ነገር ቢኖር የኢኮኖሚ ችግሮቻችንን ከቶውንም ቢሆን የማንሻገራቸው ሳይሆን እንደመንግስትና እንደ ህዝብ ከተባበርን ድህነትን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ከመሰረቱ ነቅለን ብፅግናን ማምጣት ብሎም አስተዳደራችንም ለነዋሪዎቿ ሰብዓዊ፣ ክብራዊና ቁሳዊ ፍላጎቶችን በተሻለ የምታሟላ ከማድረግ ወደኋላ የሚመልስን አንዳች ሃይል እንደሌለ ነው፡፡
ይህንንም ለማሳካት የማክሮ ኢኮኖሚ ላይ ትኩረት በማድረግ ፈጣን የኢኮኖሚ እድገትና አስተማማኝ የመካከለኛ ገቢ አቅም ለመፍጠር የሚያስችል አዳዲስ አሰራሮችን በመዘርጋትና ተቋማዊ አቅም በመገንባት ነዋሪዎቻችን በተለይም ወጣቶቻችን የስራ ፈጣሪና ከሚመነጨው ኢኮኖሚ ተሳታፊም ተጠቃሚም የሚሆኑበትን እድል እንፈጥራልን፡፡
በገጠር አርሶና አርብቶ አደሮች ከዝናብ ጥገኝነት የሚላቀቁበትና የመስኖ ልማት አቅምና በማስፋት የምግብ ዋስትናቸው እንደሚረጋገጥ እንዱሁም የእንስሳ ሀብት ልማት የውጪ ምንዛሪ እንዲያስገኝ በሚያስችል አቅጣጫ የምንሰራ ይሆናል፡፡
ግብራናችን ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ለማድረግ ከዚህ በተጨማሪም ለአስተዳደራችን የህልውና አደጋ የሆነው ጎርፍ በአረንጓዴ ልማት ስትራቴጂ ትግበራ የኢኮኖሚያችንንም የዜጎቻችንንም የመኖር ስጋት በሚቀረፍበት ደረጃ ለመከላከል በሚያስችል መልኩ ርብርብ እናደርጋለን፡፡
በታሪክ አጋጣሚ ድሬዳዋችን ከምስረታዋ አንስቶ የንግድና የኢንዱስትሪ መነሻና መድረሻ መሆኗ ከራሳችን አልፎ ለቀጠናውና ለአገራዊ የብልፅግና ጉዞ ስምረት ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታ ያላት አስተዳደር እንድትሆን አድርጓታል::
ይህን መልካም እድል በቀጣይ አሟጦ ለመጠቀም በዘርፉ የሚስተዋሉ የተንዛዛና ገዳቢ የመንግስት ቢሮክራሲን፣ የፋይናንስ እጥረትና የመሳሰሉትን ተግዳሮቶች በመፍታት እንዲሁም የግሉን ዘርፍ ሚናና አጋርነት በማሳደግ የምግብና ምግብ ነክ፣ የአግሮ ፕሮስሲንግን፣ የጨርቃ ጨርቅና አልባሳት፣ የኮንስትራክሽን ግብዓት ምርቶች እና የማዳብሪያና ኬሚካል ምርቶችን በተወዳዳሪነት በማምረት የአስተዳደሩን ነዋሪዎች ፍላጎት ማሟላትና ለሀገር ውስጥና ለውጪ ገበያ የማቅረብ አቅጣጫን ተከትለን የምንሰራ ይሆናል፡፡
የአገልግሎት ዘርፉን በተለይም የቱሪዝም ሀብት በቀላል ግብአቶችና ጥረቶች በአጭር ጊዜ ለውጥ ማምጣት የሚያስችል አቅም ያለን እንደመሆኑ ከመቶ አመት በላይ ካስቆጠረው የባቡር ትራንስፖርት አንስቶ በርካታ ሺህ አመታትን ያልቆጠሩ የዋሻ ውስጥ ስዕሎች ድረስ ለአስተዳደሩ ኢኮኖሚ ገቢ ማስገኛ እና ለነዋሪዎችን ስራ እድል መፍጠሪያ እናደርጋቸዋለን፡፡
ድሬዳዋችን የአፍሪካ ህብረት መቀመጫና ሀገራችን ኢትዮጵያ መዲና ከሆነችው አዲስ አበባ ከተማ ቀጥሎ ሁለተኛዋ ትልቋ ከተማ እንደመሆኗ ደረጃዋን የሚመጥን፣ ጊዜው የሚጠይቀውን የእድገትና የከተማ ልማት ማረጋገጥ ይጠይቀናል፡፡
ድሬዳዋችን ፅዱ፣ ለኑሮና ለልማት ምቹ እንድትሆን የመልሶ ማልማትና የማስፋፊያ ስራዎችን ለማከናወን እንዲሁም ለነዋሪዎቻችን የቤት ችግር እንዲቀረፍ የቤት ልማት በአነስተኛ ወጪና በጥራት የማከናውን አቅጣጫን ተከትሎ አስተዳደሩ የሚስራ ይሆናል፡፡
አስተዳደራችን ለኢንቨስትመንት ምቹና ሳቢ እንዲሆን በማድረግ በአስተዳደራችን ከሚመነጨው ኢኮኖሚ የሚሰበሰበው ገቢ አንድም በዲጂታል አሰራር እንዲዘምንና ገቢያችን እንዲያድግ በሌላ በኩል ከገቢ ጋር ተያይዞ ያሉ የከተማችን እድገት ጎታች የሆኑና ፍትሃዊ ያልሆኑ አሰራሮች እንዲስተካከሉ ከፊደራል መንግስት ጋር የምንሰራ ይሆናል፡፡
በማህበራዊ ዘርፍ የትምህርት ስርዓታችን ቀና አመለካከት ያለውና ሃላፊነት የሚሰማው ብቁ ዜጋ እንዲፈጥር ትምህርትና ሥልጠናን ከችሎታ እና ከአቅም ጋረ በማጣጣም አካታችና ፍትሃዊ በተለይ በመጀመሪያ ደረጃ ዕርከን የአስተዳደራችን ተማሪዎች አካባቢያቸውን በተገቢው እንዲረዱ እና እንዲገነዘቡ ባህልና እሴቶቻችንን እሚላበሱ እንዲሆን ይሰራል፡፡
የጤና አገልግሎታችን አክሞ የማዳን አቅምን የሚያሳድግ፣ ከደባል ሱሶች ነጻ የሆነ ጤናማና ቴክኖሎጂን ተጠቅሞ ዕውቀት መር ኢኮኖሚውን ሊያንቀሳቅስ የሚችል ዜጋ የመፍጠር አቅጣጫን አስተዳደሩ ይከተላል፡፡
እንዲሁም በማህበራዊ ዘርፉ ሁልጊዜም ቢሆን በህግና በአዋጅ የተደነገገ መብት ያላቸው ቢሆንም ነገር ግን ከአተገባበር አካያ ብዙ ትኩረት የሚያሰጣቸው እና እንደ አንድ ዜጋ ከሁሉም ዜጎች እኩል መብታቸው ሊረጋገጥላቸው የሚገቡ የማህበረሰብ ክፍሎች በተለይ አካል ጉዳተኞች እና አረጋውያን በአስተዳደሩ በሚሰሩ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚዊ እንዲሁም የልማት እንቅስቃሴዎች የተነፈጉትን መብት የማረጋገጥ ስራ ከነሱ ጋር በመሆን ያላቸውን እውቀትና አቅም ለአገር የሚያበረክቱበትን ሁኔታን ልዩ ትኩረት ሰጥተን እንሰራለን፡፡
ክቡራትና ክቡራን:-
በ6ተኛ አገራዊ ምርጫ የተለያየ የፖለቲካ ፓርቲዎች የተለያየ ሀሳብ ይዘን ቀርበን ግን ደግሞ ህዝብ መርጦና በውጤቱም ኢትዮጵያ እንድታሸንፍ እንደሆነው ሁሉ ድሬዳዋችንን ስለማበልፀግ ስናስብ ያለ ሁላችንም ተሳትፎና ርብርብ ሊሆን እንደማቻል ልብ እንዲባል እፈልጋለሁ፡፡
የተከበራችሁ የአስተዳደሩ ወጣቶች:-
ድሬዳዋን ከራሳችን አልፎ ለሌሎች ትበቃለች ስንል የእናንተ የወጣቶች እውቀትና ጉልበት ስራ ፈጣሪነትና ታትሮ መስራትን እንደ እምቅ አቅም ቆጥረን ነው፡፡ ውድ ወጣቶቻችን ስራን ባለመናቅና ባለመጠበቅ ከራሳችሁ አልፋችሁ ለአገራችሁ የምታስፈልጉና የምትተርፉ መሆኑን በተረዳ መንፈስ በጋራ እንድንሰራ ጥሪዬን አቀርባለሁ፡፡
የተከበራችሁ የአስተዳደሩ ሴቶች:-
ያለ እናንተ ድሬዳዋ ምንም ናት እና ድሬዳዋ የእናንተን መሻትና ፍላጎት እንድታሟላ አስተዳደሩ እንደሚሰራ ቃል እገባለሁ፡፡ እናንተም በአመራር ሰጪነትም ሆነ በልዩ ልዩ መስክ ያላችሁን ተሳትፎ እንድታጠናክሩ ጥሪዬን አቀርባለሁ፡፡
የተከበራችሁ የአስተዳደራችን የንግድ ማህበረሰብና ባለሀብቶች:-
ድሬዳዋ ሰርታችሁ የትበለፀጉባትና ተከብራ የምታስከብራችሁ እንድትሆን ግብርን በታማኝነትና በወቅቱ መክፈል ባህል ልታደርጉ ይገባል፡፡ የድሬዳዋ አስተዳደርም ነግዳችሁ እንድታተርፉ ኢንቨስት አድርጋችሁ እንድትበለፅጉ የሚስተዋሉ የመንግስት አቅም ውስኝነቶችን ለመቅረፍ፣ የሚገጥማችሁንም የፋይናንስ አቅርቦት ችግር ለመፍታት አበክረን እንደምንሰራ እየገለጽኩ እናንተም ለአስተዳደራችን ብሎም ለአገራችን እድገት የበኩላችሁን አወንታዊ አስተዋጽኦ እንደምታበረክቱ ጥርጣሬ የለኝም፡፡
የተከበራችሁ የአስተዳደራችን የመንግስት ሰራተኞች:-
የድሬዳዋ አስተዳደር ነዎሪዎች ከመንግስታቸው የሚፈለጉት አገልግሎት ያገኙ ዘንድ ከሌብነትና ከመልካም አስተዳደር ችግሮች የፀዳ በመልካም የአገልጋይነት ስብዕና ተሞልታችሁ ስራችሁን እንድታከናውኑ እያሳሰብኩ፤ ነዋሪዎቻችን በእውቀት እንዲታነፁ፤ ጤናማና አምራች እንዲሆኑ እናንተ በቅንነትና በታታሪነት ስታገለግሉ አስተዳደሩ ደግሞ ባለው አቅም ሁሉ መብትና ጥቅማችሁን ለማስከበር እንደሚሰራ ቃል እገባለሁ፡፡
የተከበራችሁ አስተዳደራችንና የፌደራል የፀጥታ አካላት:-
የአስተዳደራች ሰላም እንዲመለስ ከህዝብ ጋር ስለከፈላችሁ ከፍተኛ ዋጋ ሳላመሰግን ለማለፍ አልወድም፡፡ በቀጣይም ሠላሟ የተጠበቀ ድሬዳዋ እንድትኖረንና ለኑሮም ለኢንቨስትመትም ተመራጭ ከተማ እንዲኖረን የእናንተ ሚና ከፍተኛ ነውና ተልዕኮአችሁን በከፍተኛ ንቃት እንድታፈፀሙ ጥሪዬን ለማቅረብ እወዳለሁ፡፡
የተከበራችሁ በመላው አለም የምትገኙ የድሬዳዋ ተወላጆችና ወዳጆች የሆናችሁ የዲያስፖራ ወገኖቻችን:-
የድሬዳዋ ተወላጆችና ወዳጆች የሆናችሁ የአስተዳደራችን ዲያስፖራዎች በአካል ብትርቁም በሀሳብ፣ በገንዝብና በኢንቨስትመንት እስከዛሬ ድሬዳዋን ለመደገፍ እያደረጋችሁት ያለውን ጥረት ሳላደንቅና ሳላመሰግን ማለፍ አልፈልግም፡፡
በቀጣይም ከዚህ ቀድም በበለጠው በመንግስት አቅም የማይሸፈኑ የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉድለቶችን በመሙላት እውቀታችሁንና ገንዘባችሁን ለድሬዳዋ እድገት እንድታውሉ ጥሪ እያቀረብኩ፤ የአስተዳደሩን እገዛ የምትሹት የትኛውም ጉዳይ ሲኖር ሁሌም ከጎናችሁ እንደሚሆን ቃል እየገባሁ፤ በየአላችሁበት ድግሞ የድሬዳዋ አምባሳደር እንደምትሆኑ እምነቴ ነው፡፡
በመጨረሻም መላው የአስተዳደራችን ነዋሪ ህብረተሰብ በተለይ ወጣቱ በአስተዳደራችን ተሳትፎና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት፣ የህግ የበላይነት፤ አገራዊ አንድነት፣ ልማትና መልካም አስተዳደር የተረጋገጠበት፣ ሰብዓዊና ዴሞክራሰያዊ መብቶች የተከበሩበት እንዲሁም የንግድ፣ የኢንዱስትሪና የአገልግሎት ማዕከል እና የሠላም ተምሳሌት ሆና ድሬደዋችን እንድትቀጥል ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት በብልጽግናና በክብር የልዕልና ማማ ላይ አስተማማኝ መሠረት ላይ ለመንገባት በፍቅር እና በመተጋገዝ መንፈስ እንድንረባረብ ጥሪዬን እያቀረብኩኝ፤ መጪው የሥራ ዘመን የሠላም፣ የልማት እና የስኬት እንዲሆንልን ከልብ እመኛለሁ፡፡
አመሰግናለሁ


