የድሬዳዋ አስተዳደር ባሳለፍነው ሳምንት አዲስ መንግስት የማዋቀርና ምክር ቤቱን የመመስረት ተግባር አከናውኗል ። ይህንንም ተከትሎ የምክር ቤት አመራሮችን የመሰየም ፣ ተጠሪ መስሪያ ቤቶች የመሾም ብሎም የቢሮ ሀላፊዎችና ካቢኔዎችን የመሾም ተግባር አከናውኗል ።
በድሬዳዋ አስተዳደር ከተመሰረትው አዲስ የመንግስት ምስረታ ጋር ተያይዞ እንዲሁም በቀጣይ የሚሰሩ ስራዎችና ከነዋሪው ህብረተሰብ የሚጠበቁትን ተግባራት በማስመልከት የድሬዳዋ አስተዳደር የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ሀላፊ የሆኑት አቶ እስቂያስ ታፈሰ ለጋዜጠኞች ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል ።
በድሬዳዋ አስተዳደር አዲስ በተዋቀረው መንግስት ውስጥ 13 ካቢኔ እንጂ 15 ካቢኔ ተዋቀረ የተባለው መረጃ ትክክል እንዳልሆነና ሁለቱ ዋና ኦዲት ቢሮና የድሬዳዋ ብዙሀን መገናኛ ኤጀንሲ ለምክር ቤት ተጠሪ ሆነው በምክር ቤቱ ተሾመዋል እንዲሁም የአስተዳደሩ ካቢኔና ምክር ቤት ሌሎች ሹመቶችን እንዳሳለፈና በዚህም መሰረት በምክትል ከንቲባ ማእረግ የመንግስት ተጠሪ ሀላፊ በተመሳሳይም በአስተዳደር ደረጃና በቢሮ ሀላፊ ደረጃ ሶስት ረዳት የመንግስት ተጠሪዎች በክቡር ከንቲባው አቅራቢነት በምክር ቤቱ መሾማቸውን የድሬዳዋ አስተዳደር የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ሀላፊ የሆኑት አቶ እስቂያስ ታፈሰ ተናግረው ከዚህም አዲስ የመንግስት ምስረታው ጋር ተያይዞ ቀጣይ ስራዎች እንደሚኖሩና ይህም በዋውናነት ከምክትል ቢሮ ሀላፊዎች ጀምሮ ፅህፈት ቤት ሀላፊዎች እንዲሁም እስከ ታችኛው አመራር ድረስ ያለው ከላይኛው በተጀመረው የመንግስት ምስረታ አግባብ አደረጃጀትና አሰራርን እንዲሁም አፈፃፀምና ብቃትን እየፈተሹ በአጭር ጊዜ የሚከናውን እንደሆነና ለአስተዳደሩ ነዋሪዎችም ግልፅ እንደሚደረግም ነው አቶ እስቂያስ የተናገሩት ።
የቢሮው ሀላፊ አክለውም የድሬዳዋ አስተዳደር አዲሱ አመራርን መነሻ አድርጎ ወደ ስራ ለመግባት ያሰባቸው ጉዳዮች ከሰፊው ነዋሪ ጋር ውይይትና ምክክር የማከናወን ስራ በአጭር ጊዜ ውስጥ ተከናውኖ ቀደም ሲል የተጀመሩ ትልልቅ ስራዎች የህዝብን ውይይት ታሳቢ ባደረገና ከዛ የሚገኙ ግብአቶችን መነሻ በማድረግ የሚሻሻሉ ጉዳዮችን ለማሻሻል የአጭርና የረጅም ጊዜ እቅድ እንደተዘጋጀና ሁሉም ተቋማት የነዋሪውን ህብረተሰብ ተጠቃሚነት በተግባር ሊያረጋግጡ የሚችሉ የ 60 ቀን እቅድ እንዲያወጡና ተቋማቱ የሚያወጡት የ 60 ቀን እቅድ ወደ አስተዳደሩ ካቢኔ በመቅረብና ትኩረት በመስጠት ወደ ተግባር ለመግባት አቅጣጫ ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን አቶ እስቂያስ ተናግረዋል ።
ሌላው በድሬዳዋ አስተዳደር እድገትና እጣ-ፋንታ ላይ የሚወስኑ ጉዳዮች ላይ ከፌደራል መንግስትና እንዲሁም በአስተዳደር ደረጃ ሊሻሻሉ የሚገቡ የአወቃቀር ፣ የአሰራር ፣ የህግ ማሻሻዮችን በመለየት በአፋጣኝ የህዝብ ተጠቃሚነትን ሊያረጋግጥ በሚችሉ ጉዳዮች ላይ ርብርብ ለማድረግ እንደታቀደና ይህም የድሬዳዋ አስተዳደር ቻርተርን ከማሻሻል ጀምሮ እንዲሁም አብዛኛው የከተማው ገቢ ወደ ፌደራል መንግስት ከመሄዱ ጋር ተያይዞ ልማታችንና እድገታችን እንዳይፋጠን እንዲሁም የስራ እድል ፈጠራ ላይ በሚፈለገው ደረጃ እንዳይሆን ማነቆ እንደሆነና የጋራ ገቢ ክፍፍሉ ቢመጣ አሁን ላለንበት አዲስ ምእራፍ አጋዥ መሆኑንም ነው አቶ እስቂያስ የተናሩት ።
በተለይም በድሬዳዋ አስተዳደር የሚገኙ ወጣቶች ፣ ሴቶች ፣ ምሁራን ፣ ባለሀብቶች ፣ የሀገር ሽማግሌዎች ፣ የሀይማኖት አባቶች ፣ ነዋሪዎች በሀገር ደረጃ ለተደረገው አጠቃላይ ለውጥና ሰላም መስፈን የነበራቸው አስተዋፆ ከፍተኛ እንደነበርና በቀጣይም የተለያዩ የምክክር መድረኮች በከተማው ላይ እንደሚኖሩና እነዚህም የምክክር መድረኮች ድሬዳዋን ወደ ፊት እንዴት ማስቀጠል እንደሚገባና በዚህ ውስጥም የሁሉም ሚና እንዲኖር የማድረግና ያለ አድሎ ለማገልገል ብሎም ፍትሀዊና ለህዝቡ የቀረበ መንግስት ለመሆን በመሰራት ላይ እንደሆነና ድሬዳዋንም ለመቀየር የሁሉም ጥረት እንደሚያስፈልግም አቶ እስቂያስ ታፈሰ ተናግረዋል ።


