የድሬዳዋ አስተዳደር ካቢኔ በአዲስ መዋቀሩን ተከትሎ አዲስ አሰራሮችን ለመዘርጋትና ለመተግበር አቅዶ ወደ ስራ የገባ ሲሆን ይህንኑ ተግባራዊ ለማድረግ ይቻለው ዘንድ መስከረም 26 ባደረገው አስቸኳይ ስብሰባ የተለያዩ ውሳኔዎችን አሳልፏል፡፡
የተላለፈውን ውሳኔ ተከትሎ የድሬደዋ አስተዳደር የመንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ሃላፊ አቶ እስቂያስ ታፈሰ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡በጋዜጣዊ መግለጫቸው እንደገለጹት
1. በከተማችን ድሬዳዋ ለሚስተዋለው የትራፊክ መጨናነቅና ከዚህም ጋር የተለያዩ ወንጀሎች ምክኒያት እየሆኑ ያሉትን ከባድ ተሸከርካሪዎች ከከተማ እንዲወጡና በከተማችን የተሳለጠ የትራፊክ ፍሰት እንዲኖር እንዲሁም ከአደጋና ከወንጀል የጸዳች ከተማን እውን ለማድረግ ይረዳ ዘንድ የችግሩን አሳሳቢነት በመረዳት የአስተዳደሩ ካቢኔ ከፌደራል ትራንስፖርት ባለስልጣን በተገኘ በጀት ተገንብቶ አገልግሎት ላይ የሚውል የከባድ ተሸከርካሪ ማቆሚያ የግንባታ መሬት በጅቡቲ መግቢያ ሙዲ አነኖ በሚባል አካባቢ 12 ሄክታር መሬት እንዲሰጥ ወስኗል፡፡
2. በአስተዳዱ የአገልግሎት አሰጣጥ እና ብልሹ አሰራሮች በስፋት የሚስተዋልበትን የመሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ ለማስተካከልና ህብረተሰቡ ከተቋሙ የሚፈልገውን አገልግሎት በአግባቡ እንዲያገኝ ብሎም ውድ የሀገር ሀብት የሆነው የመሬት ሀብት ከብክነት ለመጠበቅ የአስተዳደሩ ካቢኔ ተወያይቶ ውሳኔ አሳልፏል፡፡
ውሳኔውም ከምስከረም 27 ቀን 2014 ዓ.ም ጀምሮ ተቋሙ የሚሰጣቸውን ማናቸውንም አገልግሎቶች ለአንድ ወር ያህል እንዲያቋርጥና በዚህ የአንድ ወር ጊዜም አንደኛ የተቋሙ ሰራተኞች በስራዎቻቸው ተመዝነውና ተለይተው አስፈላጊው ማስተካከያ የሚደረግበት፡፡
ሁለተኛ የመሬት ቆጠራ ስራ የሚሰራበትና
ሶስተኛ የመሬት ኦዲት ስራ የሚሰራበት ጊዜ ሆኖ ተቋሙ ያሉበትን ክፍተቶች አስተካክሎ በአዲስ መልክና በለውጥ አስተሳሰብ ወደ ስራ እንዲመለስ ውሳኔ ተላልፏል፡፡
3. በአስተዳደሩ ተጀምረው ለበርካታ ዓመታት ሳይጠናቀቁ የቆዩ ፕሮጀክቶችን በአጭር ጊዜ ውስጥ ተጠናቀው ለህበረተሰቡ የሚፈለገውን አገልግሎት እንዲሰጡ ለማድረግ የሚያስችል ውሳኔ የተሰጠ ሲሆን በዚህም መሰረት በቅድሚያ የሚሰጣቸው ፕሮጀክቶች አስፈላጊውን የበጀት ድጋፍ እንዲደረግላቸውና በአጭር ጊዜ እነዲጠናቀቁ ተወስኗል፡፡ በዚህም መሰረት
ሲቪክ ሴንተር፣ ነባሩ ስታዲየም እድሳት፣ ሁለገብ የስፖርት አካዳሚ ቴክኒክና ሙያ ተጨማሪ ኮሌጆችን ለመገንባት የተጀመረው ግንባታዎች፣ የካይዘን ኢኒስቲቲዩት ናቸው፡፡


