ታህሳስ 26 ቀን 2014 (ኢዜአ) የተረጋጋ ማክሮ ኢኮኖሚ ከማስፍን አንጻር የዋጋ ግሽበትን የመቆጣጠርና የገበያ ዋጋን የማረጋጋት ፋይዳ ያለው የ4 ሚሊዮን ኩንታል ስንዴና የ12.5 ሚሊዮን ሊትር የምግብ ዘይት ግዢ መፈጸሙ ተገለጸ፡፡
የገንዘብ ሚኒስቴርና የተጠሪ ተቋማት የመቶ ቀን እቅድ አፈጻጸም ግምገማ በተካሄደበት ወቅት እንደተገለጸው ባለፉት ጥቅምትና ህዳር ወራት የ4 ሚሊዮን ኩንታል ስንዴ ግዥ የተከናወነ ሲሆን ከዚህ ውስጥ 1,051,160 ኩንታል ስንዴ (አንድ ሚሊዮን ሀምሳ አንድ ሺ አንድ መቶ ስልሳ ኩንታል ስንዴ) ወደ ሃገር ውስጥ የገባ ሲሆን ይህም የስንዴ ዋጋ ከፍ እንዳይል የራሱ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት ታምኖበታል፡፡
የተቀረውም ስንዴ በተቻለ ፍጥነት ተጓጉዞ ወደ ሀገር ውስጥ እንደሚገባም ታውቋል፡፡
በዚሁ ወቅት የ12.5 ሚሊዮን ሊትር የምግብ ዘይት ግዢ ተፈጽሞ ወደ ሀገር ውስጥ ለማስገባት በሂደት ላይ መሆኑም ተመልክቷል፡፡
ከዚሁ ጋር በተያያዘም የምግብ ዘይትና ዱቄት ከውጭ በፍራንኮ ቫሉታ (አስመጪዎች በራሳቸው የውጭ ምንዛሪ) እንዲያስገቡ በመደረጉ የሸቀጦች ዋጋ ባለበት እንዲቀጥል ማስቻሉም ተገልጽዋል፡፡
በመሆኑም በጥቅምት ወር 2014 ዓ.ም 34.2 በመቶ የነበረ አጠቃላይ የዋጋ ግሽበት በህዳር ወር ወደ 33.0 በመቶ ዝቅ ብሏል።
የሕዳር 2014 ወርሀዊ የምግብ ዋጋ ግሽበት ካለፈው ጥቅምት 2014 ጋር ሲነጻጸር በ1.8 በመቶ የቀነሰ ሲሆን በተመሳሳይ ጊዜ ውስጥ ምግብ ነክ ያልሆኑ ሸቀጦች የዋጋ ግሽበት 1 ከመቶ የጨመረ መሆኑን የገንዘብ ሚኒስቴር መረጃ ያሳያል፡፡
- ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ
- ሀገርን በዘላቂነት እናልማ
- የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ
- ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ


