በአስተዳደራችን በኩላሊት ህመም እየተሰቃዩ የሚገኙና ህክምና ማድረግ ያልቻሉትን የህብረተሰብ ክፍሎች፤ የዲያሌሲስ ማሽን በመግዛት ከህመማቸው ለመታደግ በሚደረገው እንቅስቃሴ ውስጥ፤ በሀገር ውስጥና በውጭም ጎ-ፈንድ በመክፈት በሚደረገው ርብርብ የኢትዮጵየውያኑና ትውልደ ኢትዮጵያውያኑ፣ የድሬዳዋ ተወላጆችና ወዳጆች ተሳትፎ እጅግ የሚያስመሰግን ነው፡፡
በዚህ እንቅስቃሴ ውስጥ እያደረጋችሁት ላለው አስተዋፅኦ እና በቀጣይም ለምታደርጉት ከፍተኛ ተሳትፎና ዕገዛ በራሴና በድሬዳዋ አስተዳደር ስም፤ እንዲሁም በዚህ ህመም ስቃይ ላይ ባሉ የእኛንና የእናንተን ድጋፍ በሚጠብቁ የኩላሊት ታማሚዎች ስም ምስጋናዬን ሳቀርብ በታላቅ አክብሮት ነው፡፡
እንዲሁም የድሬዳዋ አስተዳደር በምታደርጉት ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ ከጎናችሁ መሆኑን እየገለፅኩ በዕውቀት፣ በቴክኖሎጂ ሽግግርና በሌሎችም ዘርፎች እያደረጋችሁት ያላችሁትን አስተዋጽኦ አጠናክራችሁ እንድትቀጥሉ መልዕክቴን ለማስተላለፍ እወዳለሁ።
ውድ የድሬዳዋ አስተዳደር ነዋሪዎች አስተዳደራችን በያዘው በአዲስ ምዕራፍ የጀመረውን የለውጥ እንቅስቃሴ ድሬዳዋችን ወደ ቀድሞ ስሟና ከፍታ ለማድረስ የጀመርናቸውን ዘርፈ ብዙ የልማት እንቅስቃሴዎች ከለውጡ ማግስት ጀምሮ የለውጥ አመራሩን በመደገፍና ከጎኑ በመሰለፍ እያደረጋችሁ ያላችሁት እንቅስቃሴ ምስጋና የሚቸረው ነው።
በዚህ ልዩ የክብርና የምስጋና እራት ግብዣ ላይ እንቅስቃሴው በዲያስፖራው ብቻ እንዳይቆም ሁሉን አቀፍ ትብብር ያስፈልጋል በሚል በዚህም እየተሳተፋችሁ የምትገኙና ለመሳተፍም በዝግጅት ላይ ያላችሁ በድሬዳዋ አስተዳደር ስም የላቀ ምስጋናዬን አቀርባለው፡፡
ይህ ፕሮግራም እንዲሳካ በሀገር ውስጥና በውጭ ያሉትን በማስተባበርና በማነቃቃት እንዲደግፉ በማድረግ፤ ሌት ተቀን የተረባረባችሁ ውድ የድሬዳዋ ልጆችና ወዳጆች በጠቅላላ አስተባባሪ ኮሚቴዎችን በማመስገን፤ ይህ ከአስተዳደሩ ጎን የመቆም የትብብርና የመደጋገፍ ስሜታችሁ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪዬን እያቀረብኩ ፈጣሪ ብድራችሁን ይክፈላችሁ እላለሁ።
ፈጣሪ ኢትዮጵያንና ህዝቦቿን ይባርክ


