የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የንግድና ቱሪዝም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላት የድሬዳዋ ኢንዱስትሪ ፓርክን ጎበኙ ።

    የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የንግድና ቱሪዝም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላት በዛሬው እለት በድሬዳዋ ኢንዱስትሪ ፓርክ ጉብኝት ያካሄዱ ሲሆን የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከተሰጠው ህገ-መንግስታዊ ኃላፊነት አንዱ የአስፈፃሚ ተቋማት የክትትልና ቁጥጥር ስራዎችን መስራት ሲሆን ከዚህ ጋር ተያይዞም የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በፓርኩ ውስጥ ውይይትና የመስክ ጉብኝት አካሂደዋል ።
    በተለይም የድሬዳዋ ኢንዱስትሪ ፓርክ በአቅሙ ልክ ስራዎችን እየሰራ እንደሚገኝና ባለሀብቶችን ኢንቨስተሮችን ወደ ፓርኩ ከመሳብ አንፃር የሚሰጣቸውን አገልግሎቶች እንዲሁም በፓርኩ ውስጥ ያሉትን ችግሮች በሪፖርትና በመስክ ጉብኝት መመልከታቸውን በኢፌድሪ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የንግድና ቱሪዝም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባል አቶ አብዱጁዋድ መሀመድ ተናግረዋል ።
    አቶ አብዱጁዋድ አክለውም ፓርኩ ባለሀብቶችን ለመሳብ ከፍተኛ የሆነ ዝግጅት ከመኖሩም ባለፈ የተሟላ አገልግሎት መስጠት እንደሚችልና ለአካባቢው ማህበረሰብም ተገቢውን አገልግሎት ለመስጠት ይቻል ዘንድም ለበርካታ ዜጎች የስራ እድል እንደፈጠረ አቶ አብዱጁዋድ ተናግረው ነገር ግን በኢንዱስትሪ ፓርኩ ውስጥ ባሉ ጥቃቅን ችግሮች ምክንያት ባለሀብቶች ወደ ፓርኩ መሳብ እንዳልተቻለና በቀጣይም ኢንዱስትሪ ፓርኩ በሙሉ አቅሙ ወደ ስራ ይገባ ዘንድም ከምክክር ላይ መድረሳቸውንም ነው በኢፌድሪ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የንግድና ቱሪዝም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባል የሆኑት አቶ አብዱጁዋድ መሀመድ የተናገሩት ።
    የድሬዳዋ ኢንዱስትሪ ፓርክ ባለፍት 6 ወራት በፖርኩ ውስጥ 2300 ለሚሆኑ ዜጎች የስራ እድል መፍጠር መቻላቸውን የድሬዳዋ ኢንዱስት ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ካሚል ኢብራሂም ተናግረው ከውጪ ከተላኩ ምርቶች 3 ሚሊዮን 654 ሺህ ዶላር እንዲሁም ከውጪ ይመጣ የነበረውን በሀገር ውስጥ የመተካቱ ስራ ላይ ደግሞ ወደ 4 ሚሊዮን ዶላር አካባቢ ሀገራችን ኢትዮጲያ ልታወጣ የነበረችውን ማስቀረት እንደተቻለም ተናግረዋል ።
    በፖርኩ ውስጥ 15 ሼዶች የሚገኙ ሲሆን ከነዚህም ሼዶች ውስጥ 3 ቱ ብቻ በባለሀብቶች እንደተያዙና 12ቱ ሼዶች ላይ ባለሀብቶች እንዳልገቡበትና ይሄም ችግር በዋናነት በፓርኩ ውስጥ ከፍተኛ የሆነ የውሀ ችግር ከመኖሩ በዘለለ የመልካ መንገድ ካለ መሰራት ጋር ተያይዞ ባለ ሀብቶች በፓርኩ የመሳብ ፍላጎታቸው እንብዛም መሆኑን የጠቀሱት አቶ ካሚል ኢብራሂም እነዚህንም ችግሮች ለመፍታት ይቻል ዘንድም የተለያዩ ስራዎች በመሰራት ላይ እንደሚገኝም ኃላፊው ተናግረዋል ።