የሃይማኖት አባቶች 3ኛው ዙር የኮቪድ-19 ወረርሽኝ መከላከያ ክትባትን በመከተብና ለምዕመኖቻቸው ስለ ክትባቱ ግንዛቤን በመስጠት ለዘመቻው ስኬታማነት የድርሻቸውን እንደሚወጡ ተናገሩ፡፡

    3ኛው ዙር የኮቪድ-19 ወረርሽኝ መከላከያ ክትባት ዘመቻ በአስተዳደራችን መጀመሩን ተከትሎ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ መልዕክት አስተላልፏል፡፡
    የድሬዳዋ አስተዳደር የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ዋና ሰብሳቢ ሊቀብርሃንናት ቀለመወርቅ ቢምረው ለዓለም ሃገራትም ይሁን ለሀገራችን እንዲሁም ለአስተዳደራችን የጤና እና የህይወት ስጋት የሆነው ኮቪድ-19 ወረርሽኝ የሚያስከትለውን ሞትና ህመም ለመከላከል ፈጣሪ በሰጣቸው ጥበብ ተመራማሪዎች ያዘጋጁልንን የኮቪድ-19 መከላከያ ክትባትን መከተብ አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
    ዋና ሰብሳቢው አያይዘውም እኛ የሃይማኖት መሪዎችና አባቶች ከምዕመኖቻችን ቀድመን ከትባቱን በመከተብ አርዓያ ለመሆን የተዘጋጀን በመሆኑ በሁሉም የዕምነት ተቋማት ያሉ ምዕመናን ክትባቱን እንዲከተቡ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን ብለዋል፡፡
    ሌላው መልዕክታቸውን ያስተላለፉት የሃይማኖት አባት ሼክ ዩሱፍ ሃሰን 3ኛውን ዙር የኮቪድ-19 ክትባት ለመከተብ እምነታችን የማይከለክል በመሆኑ እኛም የሃይማኖት መሪዎችና የእምነት አባቶች ለመከተብ ዝግጁ በመሆናችን ምዕመናኖቻችንም የኮቪድ-19 ወረርሽኝ መከላከያ ክትባትን በመከተብ ወረርሽኙ ከሚያስከትለው አደገኛ ህመምና ሞት ራሳቸውን እንዲከላከሉና ቤተሰቦቻቸው እንዲሁም ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎችም እንዲከተቡ ማበረታታት እንዳለባቸው ጠቁመዋል፡፡
    የድሬዳዋ ወንጌላዊያን ህብረት ሰብሳቢ እና የድሬዳዋ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ዋና ፀሃፊ በበኩላቸው ቀደምት የእምነት አባቶች ለበሽተኞች ከመፀለይና ባሻገር መድሃኒት የማድረግና የማከም ተግባራትን ይፈፅሙ የነበረ ሲሆን በዚህም ዘመን ምዕመናን የእምነት አባቶቻችንን ምሳሌ በመከተል የተዘጋጀልንን የኮቪድ-19 ክትባት በመከተብ ወረርሽኙ ከሚያስከትለው አደገኛ ህመምና ሞት ራሱንና ሊከላከል ይገባል ብለዋል፡፡
    የሃይማኖት አባቶቹ ከዚህ ቀደም የተሰጡ ተከታታይ የኮቪድ-19 ክትባቶችን መውሰዳቸውንና እንዲሁም የማጠናከሪያ ክትባት ወይንም ቡስተር ዶዝ ክትባትን መከተባቸውንም ገልፀዋል፡፡
    3ኛው ዙር የኮቪድ- 19 ወረርሽኝ መከላከያ ክትባት በአስተዳደራን በከተማና በገጠር በሁሉም የመንግስት ጤና ተቋማትና በተመረጡ የክትባት መስጫ ቦታዎች እየተሰጠ ይገኛል፡፡