ከ ሰኔ 28 እስከ ሰኔ 30 2014 ዓ.ም ድረስ የሚሰጠው የ 8 ተኛ ክፍል አስተዳደራዊ ፈተና በዛሬው እለት በድሬዳዋ አስተዳደር በከተማም ሆነ በገጠር የተጀመረ ሲሆን ይህንንም የ 8 ተኛ ክፍል ፈተናን የአስተዳደሩ ከፍተኛ አመራሮች ፈተናው በሚሰጥባቸው ትምህርት ቤቶች ላይ በመገኘትም አስጀምረውታል ።
የ 8 ተኛ ክፍል አስተዳደራዊ ፈተና ውጤታማ በሆነ መልኩ ይካሄድ ዘንድም የዝግጅት ምእራፍ ፣ የትግበራ ምእራፍና የማጠቃለያ ምእራፍ በሚል እቅድ ከማውጣት አንስቶ እቅድንም የሚያስፈፅም በምክትል ከንቲባው የሚመራ አብይ ኮሚቴ በማዋቀርና ከአብይ ኮሚቴው ስርም ሰባት ንኡሳን ኮሚቴዎች ተደራጅተው በርካታ ስራዎች መሰራታቸውን የድሬዳዋ አስተዳደር ምክትል ከንቲባና የንግድ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ሀላፊ የሆኑት አቶ ሀርቢ ቡህ ተናግረዋል ።
የ 8 ተኛ ክፍል አስተዳደራዊ ፈተና ሰላማዊ በሆነ መልኩ መጀመሩን የድሬዳዋ አስተዳደር ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ የሆኑት ክብርት ወ\ሮ ፈትሂያ አደን ተናግረው የነገ ሀገር ተረካቢ ለሆኑት ተማሪዎችም ፈተናው ጥሩ ውጤት የሚያመጡበት ፈተና እንዲሆንላቸውም ክብርት ወ\ሮ ፈትሂያ አደን መልካም ምኞታቸውን ተመኝተዋል ።
በዛሬው እለት በድሬዳዋ አስተዳደር በከተማም ሆነ በገጠር መሰጠት የተጀመረው የ 8 ተኛ ክፍል አስተዳደራዊ ፈተና ላይ 7 ሺህ 18 የሚሆኑ ተማሪዎች ፈተናቸውን እየተፈተኑ ሲሆን ይህም ፈተና በገጠር 46 ማእከላት በከተማ ደግሞ 22 ማእከላት በአጠቃላይ 68 ማእከላት ላይ ፈተናው እየተሰጠ እንደሚገኝም የድሬዳዋ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ምክትል ቢሮ ሀላፊ የሆኑት አቶ አቡበከር አዶሽ ተናግረዋል ።


