ሰኔ 28 ቀን 2014 (ኢዜአ) የድሬዳዋ ነጻ የንግድ ቀጠና የሙከራ ፕሮጀክትን በፍጥነት ወደ ስራ ለማስገባት እየተሰራ መሆኑን የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዳግማዊት ሞገስ ገለጹ።
የትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ ሚኒስቴር የድሬድዋ ነፃ የንግድ ቀጠናን በሙከራ ደረጃ ለማስጀመር እየተከናወኑ ባሉ ተግባራት ዙሪያ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት እያካሔደ ነው።
ሚኒስትሯ ዳግማዊት ሞገስ በዚህ ወቅት እንዳሉት፣ በኢትዮጵያ ነጻ የንግድ ቀጠና በማቋቋም የዓለም አቀፍ ንግዱን ለማሳለጥ እየተሰራ ነው።
የሎጂስቲክስ ስርዓቱን በመሠረታዊነት ለመለወጥ በስትራቴጂ ከታቀዱ ጉዳዮች አንዱ ነፃ የንግድ ቀጠና ማቋቋም ሲሆን ሀገሪቱ ከዘርፉ ተገቢውን ጥቅም እንድታገኝ የሎጂስቲክስ ምክር ቤት በፕሮግራም ደረጃ ጸድቋል ብለዋል።
በዚህም በሀገሪቱ በርካታ ነጻ የንግድ ቀጣናዎችን ለማቋቋመ የታቀደ ሲሆን በሙከራ ደረጃ በድሬዳዋ ያሉትን የሎጂስቲክስና የኢንዱስትሪ ፓርክ ምቹ ሁኔታዎችን በመጠቀም እንዲጀመር ከስምምነት ተደርሷል ብለዋል።
በኢትዮጵያ ነጻ የንግድ ቀጠና መመስረት በብሔራዊ ሎጂስቲክስ ስትራቴጂ ከተካተተ አንስቶ ባለፉት ሁለት ዓመታት ሰፊ ጥናት ሲካሔድ መቆየቱን ገልፀዋል።
ጥናቱ አሳማኝ ሆኖ በመገኘቱም በምክር ቤቱ ልዩ የኢኮኖሚ ቀጠናዎችን ማቋቋም እንደ አንድ የፖሊሲ ፕሮግራም ተይዟል ብለዋል።
በዚህ መሰረት የድሬዳዋ ነጻ የንግድ ቀጠና እንደ ሙከራ ፕሮጀክት በመጽደቁ አስፈላጊው ቅድመ ዝግጅት ሲደረግ መቆየቱን ገልፀዋል።
ነፃ የንግድ ቀጠናው ድሬዳዋ የሚገኘውን የኢንዱስትሪ ፓርክና ደረቅ ወደብን ከዓለም አቀፍ የአየር ትራንስፖርት፣ ከባቡርና ከመንገድ ትራንስፖርት ጋር በማቀናጀት፣ አስፈላጊ የሆኑ የባንክና የጉምሩክ አገልግሎቶችን ተደራሽ ያደርጋል።
በድሬዳዋ ነጻ የንግድ ቀጠና ትኩረት የተደረገባቸው ዘርፎች አጠቃላይ ንግድ፣ ሁሉን አቀፍ የሎጅስቲክስ አገልግሎትና የአምራች ዘርፉ መሆናቸውንም አመላክተዋል፡፡
በኢትዮጵያ በርካታ ነጻ የንግድ ቀጠናዎች አስፈላጊ መሆናቸውን የገለጹት ሚኒስትሯ እስካሁን የንግድ ቀጠና ባለመኖሩም ህብረተሰቡ ብዙ ኢኮኖሚያዊ ጉዳቶች ማስተናገዱን ገልፀዋል።
ጉዳቶቹን መቀነስ ከተቻለ ደግሞ ተጨማሪ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ለማስገኘት፤ ነጻ የንግድ ቀጠናውን በሙከራ ደረጅ በአፋጣኝ መመስረት እጅጉን አስፈላጊ እንደሚሆን ጠቁመዋል።
በጎረቤት ሃገራት ነጻ የንግድ ቀጠናዎች ያሉትን ኢትዮጵያውያን ነጋዴዎችና ሌሎች አካላትን በመሳብ ወደ ነጻ ንግድ ቀጣናው ማስገባት ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ መሆኑን አክለዋል።
የዚህ ፕሮጀክት መሳካት የኢትዮጵያን የሎጂስቲክስ ሥርዓት በማሻሻል የሀገሪቱን ዓለም አቀፍ ንግድ ስርዓት እንደሚያቀላጥፍ ገልፀዋል።
ለኢንዱስትሪና ከተሞች ዕድገት፣ ለሥራ ዕድል መስፋፋት፣ ለኑሮ ውድነት መቀነስ፣ በአጠቃላይ ለሁለንተናዊ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ከፍተኛ አስተዋጽዖ እንደሚኖረው ተናግረዋል፡፡
ነጻ የንግድ ቀጠናው ወደ ስራ እንዲገባ ባለድርሻ አካላት የሚጠበቅባቸውን ሚና እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።


