የንጹሃንን ደም በከንቱ የሚያፈስ የትኛውም ስብስብ በጀመርነው መንገድ ጉዟችንን አጠናክረን የምንቀጥል ከሆነ ይጠፋል-ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ

    አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ (ኤ ኤም ኤን) ሰኔ 30/ 2014
    የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 6ኛ ዙር 1ኛ ዓመት የስራ ዘመን 16ተኛ መደበኛ ስብሰባውን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በተገኙበት እያካሄደ ነው፡፡
    የምክር ቤቱ አባላት በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ የተለያዩ ጥያቄዎችንና አስተያየቶችን አንስተዋል፡፡
    ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ጥያቄዎች ማብራሪያ እየሰጡ ይገኛሉ፡፡
    ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በግፍ ለተገደሉ ንጹሃን ዜጎች የተሰማቸውን ጥልቅ ሀዘን በዚህ ወቅት ገልጸዋል፡፡
    እነዚህ ዜጎች ባልሰሩት ወንጀል በሀገራቸው ህይወታቸውን ለማሻሻል ደፋ ቀና ሲሉ ገዳዮች ያደረሱባቸው ጥቃት የሚያሳዝን ከመሆኑ ባለፈ ህይወታቸውን ለመታደግ በለመቻላችን እንደ ሀገር፤ መንግስት እና ህዝብ ጥልቅ ሀዘን ይሰማናል ብለዋል፡፡
    ኢትዮጵያ ከራሷ አልፋ የሌሎች ጎረቤት ሀገራትን ችግር በመፍታት የምትታወቅ ሀገር መሆኗን ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የጸጥታ ተቋማትና መንግስት ይህንን ችግር ለመፍታት ከፍተኛ ርብርብ እያደረገ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
    የንጹሃንን ደም በከንቱ የሚያፈስ የትኛውም ስብስብ ፤ሸኔም ሆነ ሌላ አሸባሪ ሃይል በጀመርነው መንገድ ጉዟችንን አጠናክረን የምንቀጥል ከሆነ ይጠፋል ነው ያሉት፡፡
    “ቡድኖቹ እሳቤያቸው ጥፋት ስለሆነ ሊፈትኑን ይችላሉ፤ ነገር ግን ማሸነፍ አይችሉም” ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፡፡
    ኢትዮጵያ ውስጥ የሚደረገው ግድያ መንግስት ስራውን ስለማይሰራና ሃላፊነቱን ስለማይወጣ ተደርጎ መወሰድ የለበትም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ህይወታቸውን ያጡ ዜጎች እንዳሉ ሆኖ መንግስት 24 ሰዓት የዜጎቹን ህይወት ለመታደግ ከፍተኛ ጥረት ያደርጋል፤በዚህም በርካታ ህይወት መታደግ ተችሏል ብለዋል፡፡
    ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፤በሚፈጠረው ችግር ሁሉ ህይወታቸውን የሚገብሩ የጸጥታ አካላት እንዳሉ መገንዘብ ተገቢ መሆኑን በመጥቀስ በየቀኑ ፖሊስ፤ወታደር እንደሚሞት ተናግረዋል፡፡
    ፖሊስ፤ ወታደሮች እና የክልል ልዩ ሃይሎች ህይወታቸውን ገብረው ዜጎቻቸውን ለመጠበቅ ጥረት እያደረጉ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
    የጠፋውን ብቻ ሳይሆን የጸጥታ አካላት ምን ያህል ህይወት እንዳዳኑ ማሰብ ያስፈልጋል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሳይከፈለው ሀገሩን ወዶና አክብሮ ህይወቱን ለሚከፍለው የጸጥታ ተቋም ክብር ሊሰጠው ይገባል ብለዋል፡፡