ከ176 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የተደረገበት ቴክኒክና ሙያ የሕንፃ ግንባታ ፕሮጀክት መጠናቀቁ ተገለፀ፡፡

    የግንባታ ፐሮጀክቱ በቴክኒክና ሙያ ትምህርት ስልጠና ኮሌጅ የተገነቡ ወርክሾፖችን፣ የመማሪያ ክፍሎችን እንዲሁም የስልጠናና የአስተዳደር ሕንፃዎችን የያዘ ሲሆን G+2 የሚሆኑ 3 ህንፃዎችን ለወርክሾፕ አገልግሎት የሚውል G+4 አንድ ህንፃ በአጠቃላይም 4 የሚሆኑ ህንፃዎች ግንባታ ሙሉ ለሙሉ መጠናቀቁን የድሬዳዋ አስተዳደር የስራ ክህሎትና ቴክኖሎጂ ልማት ቢሮ ሀላፊ አቶ ሮቤል ጌታቸው ገልፀዋል፡፡
    በፕሮጀክቱ ግንባታ መጀመሪያ ላይ አንዳንድ ችግሮች በመከሰታቸው ፕሮጀክቱ በተያዘለት የጊዜ ገደብ መጠናቀቅ እንዳልቻለ ሀላፊው ተናግረዋል፡፡ ይህንንም ችግር ለመቅረፍ የአስተዳደሩ ካቢኔ በወሰነው ውሳኔ መሠረት የነበሩትን ኮንትራክተሮች ውላቸው ተቋርጦ የተሻለ አፈፃጸም ላላቸው ኮንትራክተሮች ተሰጥቷል፡፡ በዚህም በአጭር ጊዜ ውስጥ ፕሮጀክቱ ሙሉ ለሙሉ ተጠናቆ ለምርቃት መድረሱን ሃላፊው ተናግረዋል፡፡
    እንደ ሀላፊው ገለፃ የፕሮጀክቱ ግንባታ ለ240 እና ከዛ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች ቋሚና ጊዜያዊ የስራ ዕድል ፈጥሯል፡፡ ፕሮጀክቱ 78ሺ ካሬሜትር ላይ ያረፈ ሲሆን እንደ አጠቃላይ ከጥራትና አላማንም ከማሳካት አንፃር ውጤታማ ፕሮጀክት ነው፡፡
    በዚህም አሁን ላይ ያለውን አንድ ወርክሾፕ ለ40 ተማሪዎች የሚያገለግለውን የሰልጣኝ ጥምርታ በዚህ ፕሮጀክት ግንባታ የተማሪዎቹ ጥምርታ ወደ ሰላሳ እንዲሆን እንደሚያስችልም ሀላፊው አንስተዋል፡፡ በተጨማሪም ይህ ፕሮጀክት በመጠናቀቁ የሰልጣኝ ቅበላ አቅሙም ከ2ሺ በላይ እንደሚሆን ተናግረዋል፡፡
    ይህም ደግሞ ለድሬዳዋ ብቻ ሳይሆን ለአጎራባች የቴክኒክና ሙያ ስልጠና ተማሪዎች ከፍተኛ ጥቅም ይሰጣል ሲሉ ገልፀዋል፡፡
    በየአመቱ እየጨመረ የመጣውን የተማሪዎች ቁጥር በአግባቡ ማስተናገድ የሚያስችል ተቋም መገንባት አስፈላጊ መሆኑን ተናግረው በእውቀትና በክህሎት ብቁ የሆኑ ሰልጣኞችንም ለማፍራት ይቻል ዘንድ ፕሮጀክቱ ትልቅ ሚና እንዳለው አቶ ሮቤል ተናግረዋል፡፡
    በመጨረሻም የቴክኒክና ሙያ ዘርፍ ትልቅ ዘርፍ እንደመሆኑ ወጣቶች ወደዚህ ዘርፍ መጥተው እውቀትን እንዲቀስሙ አቶ ሮቤል ጥሪ ያስተላለፉ ሲሆን መንግስት፣ ባለድርሻ አካላትና ህብረተሰቡም ከጎናቸው እንዲሆኑ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡