በ50 ሚሊየን ብር ካፒታል የተገነባው የአብስራ ኢንዱስትሪያል ኮምፕሊክስ የኦክስጂን ጋዝ ማምረቻ ፋብሪካ ዛሬ ክቡር ከንቲባ ከድር ጁሃር፣ ም/ከንቲባ እና የንግድ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ሀላፊ አቶ ሀርቢ ቡህ፣ በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የመንግስት ተጠሪና የብልፅግና ፓርቲ የድሬዳዋ ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት ሀላፊ አቶ ኢብራሂም ዩሱፍ፣ እንዲሁም የአብስራ ኢንዱስትሪያል ኮምፕሊክስ የኦክስጂን ጋዝ ማምረቻ ፋብሪካ ባለቤት የሆነው ወጣት የአብስራ በለጠ በጋራ በመሆን መርቀውታል፡፡
ክቡር ከንቲባ ከድር ጁሃር በምርቃት ስነ ስርዓቱ ላይ እንደተናገሩት ወጣቶችን ከደገፍናቸውና ካበረታታናቸው ከዚህ የበለጠ ስራ እንደሚሰሩ ወጣት ያብስራ በለጠ ማሳያ ነው ብለዋል አክለውም የአብስራ ኢንዱስትሪያል ኮምፕሊክስ ፋብሪካ ለሚሮሩት ቀጣይ ስራዎች አስተዳደሩ አቅም በፈቀደ መልኩ ድጋፍ እንደሚደረግለት ተናግረዋል፡፡ አስተዳደሩ በቀጣይ በኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ የመስሪያ ቦታዎችን ለማመቻቸት ጥረት ይደረጋል ብለዋል፡፡
የአብስራ ኢንዱስትሪያል ኮምፕሊክስ የኦክስጂን ጋዝ ማምረቻ ፋብሪካ ለከተማችን በአይነቱ የመጀመሪያ የሆነና የመጨረሻ ቴክኖሎጂ የተገጠመለት መሆኑን የፋብሪካው ባለቤት ወጣት የአብስራ በለጠ ተናግሯል፡፡ ወጣት የአብስራ አክሎም በቀን 520 ሲሊንደር ኦክስጅን ጋዝ፣ 270 ሲሊንደር የአሲቴልን ጋዝ እንዲሁም 360 ሲሊንደር የናይትሮጅን ጋዝ የማምረት አቅም መኖሩን ጠቅሷል፡፡
የአብስራ ኢንዱስትሪያል ኮምፕሊክስ በቀጣይ የድሬዳዋን እድገትና ብልፅግና የሚያረጋግጡ፣ ለከተማዋ ወጣቶች የስራ እድል የሚፈጥሩ በርካታ ስራዎችን ለመስራት ትልቅ ራዕይ ሰንቆ እየተንቀሳቀሰ መሆኑ ተነግሯል፡፡
ድርጅቱ ከአስተዳደሩ ጎን በመቆም ድሬዳዋን ወደ ላቀ እድገት ደረጃ ለማድረስ የተጀመረው ጥረት እውን እንዲሆን የበኩሉን አስተዋፅኦ ለማበርከት ዝግጁ መሆኑን ተነግሯል፡፡
ፋብሪካው ተገንብቶ እንዲበቃ የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር የተለያዩ ተቋማት በምንም የማይተካ ድጋፋቸውን በመስጠት ከፍተኛ ሚኛ መጫወታቸውን የአብስራ ኢንዱስትሪያል ኮምፕሊክስ የኦክስጂን ጋዝ ማምረቻ ፋብሪካ ባለቤት የሆነው ወጣት የአብስራ በለጠ በመድረኩ ላይ ገልፀዋል፡፡
የድራደዋ አስተዳደር ጤና ቢሮ ሃላፊ ወ/ሮ ለምልመ በዛብህ በበኩሏ ፋብሪካው ለጤናው ዘርፍ አስፈላጊ ግብአት የሆነውን የኦክሲጅን ምርት በአነስተኛ ዋጋ በቅርበት ማግኝት ስለሚያስችል ለዘርፉ የሚሰጠው ጠቀሜታ የጎላ መሆኑን አስረድተዋል።


