አሸባሪው ህወሃት ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ የማያዳግም እርምጃ ሊወሰድበት እንደሚገባ በአስተዳደሩ የሚገኙ የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ገለጹ፡፡
በዛሬው እለት በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ በአስተዳደሩ ስር ለሚገኙ የፖለቲካ ፓርቲ የጋራ ምክር ቤት አመራሮች ጋር ውይይት ተደርጓል፡፡
በውይይት መድረኩም የብልጽግና ፓርቲ ድሬዳዋ ቅ/ጽ/ቤት ምክትልና የፖለቲካ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ሻኪር አህመድ በውይይቱ እንደተናገሩት የሽብር ቡድኑ በተደጋጋሚ ጊዜ ሀገሪቷን ለማፍረስ ተልእኮ አንግቦ ቢንቀሳቀስም የትኛውም ምድራዊ ሀይል ኢትዮጵያን ማፍረስ እንደማይችል በተግባር ማሳየት የቻልንበት መሆኑን ገልጸዉ አሸባሪው ህወሃት ደም ማፋሰስ እና ጦርነት አማራጭ አድርጎ ለአለም ህዝብ ሰላም ማምጣትን እንደማደናገሪያ በማድረግ እና በማሳየት ጊዜ ገዝቶ ወደ ጦርነት የመግባት የማዘናጋት ስራዎችን እየሰራ መቆየቱን ተናግረዋል፡፡
ዛሬም በግልጽ ጦርነት ከፍቶ ንፁሀንን ለሞት እና ለማፈናቀል ምክኒያት ሆኗል ብለዋል፡፡
ሀገራችንም ተገዳ በገባችበት ጦርነት ውስጥ አሉ የተባሉ የሰላም አማራጮችን ብትጠቀምም በየጊዜው ለሰላም የዘረጋቸውን እጅ በመንከስ ሀገርን ለማፍረስ ቆርጦ መነሳቱን ያረጋገጠ የሽብር ቡድን መሆኑን አስመስክሯል ያሉት ሀላፊው ለዚህም የመጨረሻ አማራጭ የኢትዮጵያ መንግስት ተመጣጣኝ የሆነ እርምጃ ለመውሰድ በአቅምም ራሱን በቴክኖሎጂ፣ በሰው ሀይል እና ዘመናዊ መሳሪያዎችን በመጠቀም ከየትኛውም ጊዜ ከፍ ያለበት ደረጃ ላይ መድረሱን ተናግረዋል፡፡
ከኢ.ሀ.ፓ ተወካይ የሀገር ጉዳይ የጋራ አጀንዳችን ነው በሀገሪቱ ወቅታዊ ጉዳይ ላይ ለመምከር ከጋራ ምክር ቤቱ ጋር ውይይት ለማድረግ በዚህ መልኩ ሀሳብ እንድንሰጥ መደረጉ የሰለጠነ የዳበረ ዲሞክራሲያዊ አካሄድ መሆኑን ተናግረው አሸባሪው ህውሃት በፓርላማ ደረጃ አሸባሪ ተብሎ የተፈረጀ ድርጅት በግልጽ ሀገር ለማፍረስ የተሰማራ ሽፍታ መሆኑ የተረጋገጠ በመሆኑ ድርድር የማያስፈልገው ግብአተ መሬቱ እሰኪፈጸም መታገል ይገባል ብለዋል፡፡
ከኢ.ዜ.ማ ተወካይ መንግስት የሰላም አማራጮችን ከልክ በላይ ነው የተጠቀመው ህውሃት በተለያዩ ጊዜ ሉአላዊነታችንን በመድፈር በዜጎች ላይ የሚያደርሳቸው ጥቃቶች ለሰላም ዝግጁ አለመሆኑን ማሳያ ናቸው ለዚህም ተመጣጣኝ አጸፋ ምላሽ መንግስት ሊሰጥ ይገባል ብለዋል፡፡
ከአ.ብ.ን ተወካይ፡- መንግስት ለሰላም ያለውን ቁርጠኝነት ቢያሳይም አሸባሪው ህወሃት ለሰላማዊ ድር,ድር ፍላጎት አለመኖሩ በግልጽ ያሳየበት፤በሰላማዊ መንገድ ተወያይቶ ሰላም ማምጣትና ለህዝብ ማሰብ የህወሃት ባህሪ አለመሆኑን ተገንዝቦ መንግስት የህወሃትን ቀቢጸ ተስፋ በማያዳግም መልኩ ለመጨረሻ ጊዜ እርምጃ ሊወስድ እንደሚገባ የፖለቲካ ፓርቲዎች አስረድተዋል፡፡
በሰላም ለማ
ፎቶ፡- ይድነቃቸው አብርሀም


