|በድሬዳዋ ከተማ በ5 ቢሊዮን ብር ወጭ በሀገር ውስጥ ባለሀብት ሙሉ ለሙሉ የሚለማ የኢንዱስትሪ ፓርክ መገንባት የሚያስችል ስምምነት ተፈረመ።

የኢንዱስትሪ ፓርኩ በኢትዮጵያ የመጀመሪው በሀገር ውስጥ ባለሀብት የሚለማ ብቸኛው ፓርክ እንደሆነ ተገልጿል።
የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ‘ሬዳዋ ሞተርስ ኢንዱስትሪ’ ከተሰኘ ሀላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ ጋር በድሬዳዋ የኢንዱስትሪ ፓርክ ለማልማት የሚያስችል ስምምነት ተፈራርሟል።
ስምምነቱን ምክትል ኮሚሽነር አቶ ዳንኤል ተሬሳ እና የ’ሬዳዋ ሞተርስ ኢንዱስትሪ’ ባለቤትና ዋና ስራ አስፈፃሚ ኢንጅነር ታደሰ አድማሱ ተፈራርመዋል።
የኢንዱስትሪ ፓርኩ በ116 ሄክታር መሬት ላይ የሚያርፍ ሲሆን በኢትዮጵያ 9ኛው የኢንዱስትሪ ፓርክ ይሆናል ተብሏል።
ምክትል ኮሚሽነር አቶ ዳንኤል ተሬሳ በስምምነት ስነ-ስርዓቱ ላይ እንዳሉት ፓርኩ ሀገራዊ ምርቶችን ለማስፋፋትና ለማዘመን ይረዳል ብለዋል።
ሀገራዊ የውጭ ምንዛሬ ገቢ እንዲጨምር እና አጠቃላይ የኢኮኖሚ እድገት ለማምጣት በሚደረገው ጥረት ውስጥ የራሱ የሆነ አስተዋፆ እንዳለውም እክለዋል።
የሬዳዋ ሞተርስ ኢንዱስትሪ ባለቤትና ዋና ስራ አስፈፃሚ ኢንጅነር ታደሰ አድማሱ በበኩላቸው ድርጅታቸው በሀገሪቱ ኢንዱስትሪው ልማት እንቅስቃሴ ትልቅ ለውጥ ለማምጣት እየሰራ ነው ብለዋል።
በዚህም በድሬዳዋ ከተማ በ5 ቢሊዮን ብር ወጭ የኢንዱስትሪ ፓርክ ለመገንባት ስምምነት ማድረጉን ገልፀዋል።
ኢንዱስትሪ ፓርኩ ግንባታው ሙሉ በሙሉ ሲጠናቀቅ በውስጡ ከ23 በላይ ፋብሪካዎች የሚኖሩት መሆኑን ገልፀዋል።
የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ከድር ጁሀር በበኩላቸው ድሬዳዋ ከተማ ባለው አስተማማኝ ሰላም ምክንያት የኢንቨስትመንት አማራጭ እየሆነ መጥቷል ብለዋል።
የኢንዱስትሪ ፓርኩ መገንባት ለከተማዋ ወጣቶች የስራ እድል የሚፈጥርና የውጭ ምንዛሬ ግኝት በመጨመር ለከተማዋ እድገት አስተዋፆው የጎላ መሆኑን ነው የተናገሩት።
የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ታረቀኝ ቡሉልታ የኢንዱስትሪ ፓርኩ ግንባታ የ’ኢትዮጵያ ታምርት’ ንቅናቄ የሚያግዝ ነው ብለዋል።
የሀገር ሉዓላዊነት ለማስከበር ራስን መቻል አማራጭ የሌለው ጉዳይ በመሆኑ ሀገራዊ ምርቶችን ለማሳደግ መንግስት በትኩረት ይሰራል ብለዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።