ጳጉሜ 1 የበጎ ፍቃድ ቀንን ምክኒያት በማድረግ የደም ልገሳ መረሃ-ግብር በአስተዳደራችን ምክር ቤት ጊቢ ውስጥ ተካሄዷል፡፡
የድሬዳዋ አስተዳደር ክቡር ከንቲባ አቶ ከድር ጁሃር፣ የአስተዳደሩ ከፍተኛ አመራሮችና፣ የተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች ‹‹ጳጉሜን በመደመር›› በሚል መሪ ሃሳብ ከአምስቱ የጳጉሜ ቀናት ክንውኖች አንዱ የሆነውን የበጎ ፍቃድ ቀንን ምክኒያት በማድረግ የበጎ ፍቃድ ደም ልገሳ አከናውነዋል፡፡
ክቡር ከንቲባ ከድር ጁሃር በበጎ ፍቃድ ደም ልገሳ መረሃ-ግብሩ ላይ ባስተላለፉት ምልዕክት እናቶችና፣ ህፃናት እንዲሁም የሀገራችንን ሰላም ለመስከበር በግንባር የሚገኙ የፀጥታ ኃይሎችና፣ ሌሎችም ደም የሚያስፈልጋቸው ዜጎች በደም እጦት ምክኒያት መሞት ስለሌለባቸው በዚህ የበጎ ፍቃድ ቀንም ይሁን በሌሎች ቀናት ደማችንን ለወገናችን በመለገስ ህይወት የማዳን በጎ ተግባር ልንፈፅም ይገባል ብለዋል፡፡
የአስተዳደሩ ጤና ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ለምለም በዛብህ በበኩላቸው ክቡር ከንቲባችን ግንባር ቀደም በሆኑበትና ሌሎችም የአስተዳደሩ አመራሮች በተገኙበት የተከናወነው ይሄው የበጎ ፍቃድ ደም ልገሳ መረሃ-ግብር ላይ በመገኘት በበጎ ፍቃድ ደም የለገሱትን ሁሉ አመስግነው በተለያዩ ምክኒያቶች የሚጋጥመውን የደም እጥር ችግር ለመቅረፍ እንዲህ ያለው ተነሳሽነት እጅግ የሚፈለግ መሆኑንን ተናግረዋል፡፡
ኃላፊዋ ጨምረውም በቀጣይም የደም እጥረት እንዳያገጥመን የተቋማት አመራሮች የየተቋማት ሠራተኞችን በማሳመንና ደም ባንካችንን ፕሮግራም በማስያዝ በቋሚነት ደም እንዲለግሱ አቅጣጫ የተቀመጠ ሲሆን አመራሩም በተመሳሳይ በቋሚነት ደም እንዲለግስ መግባባት ላይ የተደረሰ ሲሆን ደም የመለገስ የበጎ ፍቃድ ሥራ በገንዘብ የማንተምነውና በተለይ ማን መቼ ደም እንደሚያስፈልገው ስለማይታወቅ ደም መለገስ የሚችል ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል የዚህ በጎ ተግባር አካል ሊሆን ይገባል ብለዋል፡፡
‹‹ጳጉሜን በመደመር›› በሚል መሪ ሃሳብ በሀገር አቀፍ ደረጃ የሚከናወኑት እነዚሁ ተግባራት ጳጉሜ 1 የበጎ ፍቃድ ቀን፣ ጳጉሜ 2 የአምራችነት ቀን፣ ጳጉሜ 3 የሰላም ቀን፣ ጳጉሜ 4 የአገልጋይነት ቀን፣ እንዲሁም ጳጉሜ 5 የአንድነት ቀን በሚል ስያሜ የተለያዩ ተግባራት ይከናወኑባቸዋል፡፡


