የድሬዳዋ ጨርቃ ጨርቅ ፉብሪካ በግማሽ ቢሊየን ብር ወጪ አዳዲስ የጨርቃ ጨርቅ ማሽኖችን በመትከል ወደ ስራ አስገባ ።

    በ 1934 ዓ.ም በአፄ ኃይለስላሴ ዘመነ መንግስት እንደተገነባ የሚነገርለት የድሬዳዋ ጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ አማ በወቅቱ የተለያዩ ክሮችን ፣ አንሶላዎችን ፣ አቡጀዲዎችንና ሌሎች ምርቶችን በማምረት ከሀገር ውስጥ ገበያ በተጨማሪም ለአውሮፖ ሀገራትም ጭምር ያቀርብ ነበር ። ይህም ፋብሪካ በተለያዩ ምክንያቶች ተገቢውን ጥገናና አዳዲስ ማሽኖች ሳይሟሉለት ለኪሳራ ተዳርጎ ቆይቷል ።
    በፕራይቬታይዜሽን ህግ መሠረት ከልማት ባንክ በ 160 ሚሊየን ብር ወጪ የድሬዳዋ ጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካን የገዛው ሬዳዋ ሞተርስ ሀላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር በግማሽ ቢሊየን ብር ወጪ አዳዲስ ማሽኖችን የተተከለበት ሲሆን ማሽኖቹም ጥሬ ጥጡን የሚያባዝትና የሚፈትሉ እንዲሁም ለተለያዩ ውፍረት ላላቸው የክር ምርት ሂደት የሚያዘጋጁም ናቸው ።
    የድሬዳዋ ጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካም በዛሬው እለት የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ከድር ጁሀርን ጨምሮ የሬዳዋ ሞተርስ ሀላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ባለቤት የሆኑት ኢ/ር ታደሰ አድማሱ ፣ የኢትዮጲያ ልማት ባንክ ፕሬዝዳንት ዶክተር ዩሀንስ አያሌው ፣ የኢትዮጲያ የልማት ድርጅቶች ይዞታ አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር አቶ ሀብታሙ ሀይለሚካኤል እንዲሁም ከፍተኛ የአስተዳደሩ አመራሮችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት ተመርቋል ።
    በዚሁም የምርቃት መርሀ-ግብር ላይ በመገኘት ንግግር ያደረጉት የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ከድር ጁሀር የድሬዳዋ ጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ በድሬዳዋ ብቻ ሳይሆን በኢትዮጲያም ጭምር በጨርቃ ጨርቅ ፈር ቀዳጅ ፋብሪካ እንደነበር ተናግረው ለረጅም አመታት ምንም አይነት አገልግሎት ሳይሰጥ ቆይቶ የነበረውን የጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ አሁን ላይ ኢ/ር ታደሰ አድማሱ ተረክቦ በውስጡ የነበሩትን ማሽኖችን በአዲስና ዘመናዊ ማሽኖች ከውጪ በማስገባትና በመተካት ወደ ስራ በማስገባቱ የተሰማቸውን ደስታ ክቡር ከንቲባው በእለቱ ገልፀዋል ።
    የድሬዳዋ ጨርቃ ጨርቅ ፈብሪካን ዘመናዊ በሆኑ ማሽኖች በማደራጀትና ከ 650 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ በማውጣት ለዛሬው የምረቃ ስነ-ስርአት መብቃቱን የሬዳዋ ሞተርስ ሀላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ባለቤት የሆኑት ኢ/ር ታደሰ አድማሱ ተናግረው ፋብሪካው በአሁኑ ሰአት የሚያመርታቸው ምርቶችን በአለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪነት ያለው ጥራቱን የጠበቀ የክር ምርቶችን እንደሚያመርት ተናግረዋል ።
    የሬዳዋ ሞተርስ ሀላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ባለቤት የሆኑት ኢ/ር ታደሰ አድማሱ ቀደምት የሆነውንና ታሪካዊውን የድሬዳዋ ጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካን ወደ ቀድሞ ክብሩ ለመመለስ ያደረግውን አስተዋፆ የኢትዮጲያ ልማት ባንክ ፕሬዝዳንት የሆኑት ዶክተር ዩሀንስ አያሌው አድንቀው የልማት ባንክ በቀጣይም ለድሬዳዋ አስተዳደር እድገትና ብልፅግና ከአስተዳደሩ ጎን በመሆን እንደሚሰራም ተናግረዋል ።
    የድሬዳዋ ጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ በኢትዮጲያ የኢንዱስትሪ ታሪክ ውስጥ ትልቅ ታሪክ ያለው እንደሆኑና ይህንንም ፋብሪካ በዘመናዊ መልክ ወደ ስራ እንዲገባ በመደረጉ መደሰታቸውን የኢትዮጲያ የልማት ድርጅቶች ይዞታ አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር አቶ ሀብታሙ ሀይለሚካኤል ተናግረው በቀጣይም በጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ ውስጥ ለሚሰሩት ስራዎች ሁሉም የበኩሉን አስተዋፆ ሊወጡ እንደሚገባም አቶ ሀብታሙ ተናግረዋል ።
    በድሬዳዋ ጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ ውስጥ በ 5 ነጥብ 4 ቢሊየን ብር ወጪ የጋርመንት ፋብሪካ ለማቋቋም የመሠረት ድንጋይ የተጣለ ሲሆን ይህም ፋብሪካ ተገንብቶ ወደ ስራ ሲገባም የተለያዩ ጅንሶችን ፣ የተማሪ ዩኒፎርሞችን ፣ ሸሚዞችን ፣ ቲሸርቶችን ካልሲዎችን ፣ የውስጥ ሱሪዎችን እንዲሁም ከፍተኛ የሆነ የውጪ ምንዛሬን ሊያስቀር የሚችል የሀገር መከላከያ የደንብ ልብሶችን እንደሚያመርትምና በሁለት አመት ጊዜ ውስጥ ተገንብቶ እንደሚጠናቀቅም ያገኘነው መረጃ ያመላክታል ።
    በአለማየሁ አበበ ።
    ፎቶ :- በይድነቃቸው አብርሀም ።