ዲዛይነር ሳራ መሀመድ ለ 5 መቶ ህጻን ተማሪዎች የዩኒፎርም ድጋፍ አደረገች ለምስራቅ ጀግኖች አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እና ለከዚራ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ባጠቃላይ ለአምስት መቶ ለሚሆኑ ህጻን ተማሪዎች በዛሬው እለት በምክትል ከንቲባው ቢሮ ውስጥ ድጋፍ ተደረገ፡፡

    በድጋፍ ስነ ስርዓቱ ላይ ተገኝተው መልዕክት ያስተላለፉት የድሬዳዋ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ሀላፊ ወ/ሮ ሙሉካ መሀመድ እንደተናገሩት ዲዛይነር ሳራ እያደረገች ላለው ድጋፍ በራሳቸውና በትምህርት ማህበረሰቡ ስም አመስግነው ለ500 ለተማሪዎቹ ሙሉ ዩኒፎርም ድጋፍ መደረጉን ተናግረዋ፡፡
    አንድም ተማሪ በትምህርት ቁሳቁስ ምክንያት ከትምህርት ገበታቸው መቅረት የለባቸውም ብለን አቅደን ከምንቀሳቀስባቸው አንዱ ከደብተርና ከብዕር ባለፈ ዩኒፎርም ለሌለው ተማሪ ድጋፍ ማሰባሰብ ነው፤ ያሉት ወ/ሮ ሙሉካ ዲዛይነር ሳራ በቀጣይ ከተማሪዎች ምገባ ጋር ተያይዞ ከትምህርት ቤሮ ጋር ሰፊ ስራ እየሰራች ያለችበት ሁኔታ አለ ብለዋል፡፡
    ተማሪዎች በአግባቡ ትምህርታቸውን እንዲማሩ መጠነ ማቋረጥንና፣ መጠነ መድገምን በመቀነስ ጥራት ያለው ትምህርት በመስጠትና ተማሪዎች አመርቂ ውጤት እንዲያመጡ ተግተን ለመስራት ተዘጋጅተናል ብለዋል፡፡
    ወ/ሮ ሙሉካ አክለውም ዋናው ትልቁ አላማ ተማሪዎች ድጋፍ ወስደው ትምህርት መጀመር ብቻ ሳይሆን እስከመጨረሻው የዓመቱን ትምህርታቸውን በጥሩ ውጤትና በጥሩ ስነ ምግባር መማር እንዳለባቸው ጨምረው ገልጸዋል፡፡
    ለህጻን ተማሪዎቹ የዩኒፎርም ድጋፍ ያደረገችው ዲዛይነር ሳራ መሀመድ እንደ ድሬዳዋልጅነቴ በሙያዬ ያደረኩት ድጋፍ ነው፤ ሁሉም በሙያው ባለው የስራ መስክ ቢተባበር ድሬዳዋን ከዚህ የበለጠ መደገፍ ይቻላል ብላለች፡፡
    በናፍቆት ድሬ ሳምንት ላይ ብዙ እንግዶች ድሬን እንዲጎበኙ አድርገናል ያለችው ዲዛይነር ሳራ የህክምና ቁሳቁሶች ላይ ድጋፍ መደረጉን ተናግራለች፡፡ ይህ ድጋፍ በቂ አይደለም ያለችው ዲዛይነሯ ድሬዳዋ ብዙ ሰታናለች ውለታዋን እጥፍ አድርገን መመለስ አለብን ይሄን ለማድረግ ጊዜው አሁን ነው፡፡
    በአንድነት ተሸምነን ድሬዳዋን ጥሩ ደረጃ ላይ ማድረስ ይጠበቅብናል አብረን ብንሰራ፣ አብረን ብንቆም በአጭር ጊዜ ውስጥ አስተዳደራችንን መለወጥ እንችላለን ብላለች፡፡
    ሌላው በዩኒፎርም ድጋፍ ስነ ስርዓቱ ላይ ተገኝተው መልዕክት ያስተላለፉት የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ጽ/ቤት ሀላፊ አቶ ገበየሁ ጥላሁን ናቸው፡፡ አቶ ገበየሁ እንደገለፁት በጎነትን በማሰብ አስተዳደሩ ላይ እየተደረጉ ያሉ ድጋፎችን ማበረታታት ይገባል ብለዋል፡፡
    ህጻን ተማሪዎችን መደገፍ ማበረታታችን የድሬዳዋን ልማት ብቻ ሳይሆን የሀገር እድገትና ብልፅግናን ከማፋጠን አኳያ ትልቅ ድርሻ ይኖረዋል፡፡ እንደ ሳራ ያሉ እህቶችን ያብዛልን ያሉት አቶ ገበየሁ ላደረገችው ድጋፍ በከንቲባ ጽ/ቤትና በራሳቸው ስም አመስግነዋታል፡፡
    በበድሉ ሀይሌ
    ፎቶ፡- በሰላም አበበ