የድሬደዋ አስተዳደር ምክር ቤት ቋሚ ኮሚቴዎች ከተቋማት ጋር የስራ እቅድ ውል ተፈራረሙ የድሬደዋ አስተዳደር ምክር ቤት እና የምክር ቤቱ ቋሚ ኮሚቴዎች በድሬደዋ አስተዳደር ቻርተር ቁጥር 416/1996 አንቀጽ 12 እና በምክር ቤቱ የአሰራርና የአባላት ስነ-ምግባር ደንብ ቁጥር 11/2009 መሰረት የድሬደዋ አስተዳደር ምክር ቤት ቋሚ ኮሚቴዎች በአስተዳደሩ ከሚገኙ የአስፈጻሚ ተቋማት ጋር የ2015 ዓ.ም የስራ እቅድ ውል የተፈራረሙ ሲሆን በስራ እቅድ ውል ፊርማው ላይ የድሬደዋ አስተዳደር ምክር ቤት አፈ ጉባኤ የተከበሩ ወ/ሮ ፈትሂያ አደን፤የድሬደዋ አስተዳደር ከንቲባ የተከበሩ አቶ ከድር ጁሀር፤ የድሬደዋ አስተዳደር ምክር ቤት ቋሚ ኮሚቴዎችና የድሬደዋ አስተዳደር የቢሮ ሀላፊዎች ተገኝቷል፡፡

    የውል ሰነዱን ያቀረቡት የድሬደዋ አስተዳደር ምክር ቤት ፅ/ቤት የህግ አወጣጥ ክትትልና ቁጥጥር ሙያዊ ድጋፍ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ቴውዎድስ ባቹሬ ሲሆኑ የውሉ አላማ የምክር ቤቱን እና የምክር ቤቱን ቋሚ ኮሚቴዎች በተቋማት ዓመታዊ እቅዶችና አተገባበራቸው ላይ የሚያደርጉት የክትትልና ቁጥጥር ስራዎች በላቀ ደረጃ ውጤታማ፤ ግልጽነትና ተጠያቂነት የተረጋገጠባቸው ማድረግና አስፈላጊነቱና ጠቀሜታውም ቋሚ ኮሚቴዎች በበጀት ዓመቱ የታቀዱ የተቋማትን ግቦች እና ዋና ዋና ተግባራት ቆጥረው ለመረከብ እና አፈጻጸማቸውን ለመከታተልና ለመቆጣጠር ያስችላቸዋል ተብሏል፡፡በአጠቃላይ ተቋማት በበጀት ዓመቱ ባቀዱት እና በጸደቀላቸው እቅድ መሰረት የስራ ተፈጻሚነቱና ውጤታማነቱ እንዲረጋገጥ በአስተዳደሩ የልማትና መልካም አስተደዳር ለማስፈን እና ህብረተሰቡ ከመንግስት ጎን በመሆን ሚናውን መጫወት እንደሚገባ በፊርማ ስነስርአቱ ላይ ተገልጿል፡፡
    © ም/ቤት ህዝብግንኙነት ክፍል