በድሬዳዋ አስተዳደር ያለውን የድንገተኛ አደጋ የህክምና አገልግሎትን በከፍተኛ ደረጃ ያሻሽለዋል ተብሎ የታመነውና በድሬዳዋ አስተዳደርና በጤና ሚኒስቴር በተመደበ 15 ሚሊዮን ብር በሚጠጋ ወጪ ለድንገተኛ አደጋ አስፈላጊውን የሆነ የህክምና አገልግሎት ሊሰጡ የሚችሉ የህክምና መሳሪያዎችና የጤና ባለሞያዎችን ያሟላው የኢትዮ-ፈረንሳይ የድንገተኛ አደጋ ህክምና ማእከል በዛሬው እለት በይፋ ተመርቋል ።
በዚሁም የምርቃት ስነ-ስርአት ላይ በመገኘት ንግግር ያደረጉት የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ከድር ጁሀር በድሬዳዋ አስተዳደር በዛሬው እለት ለምርቃት የበቃው የኢትዮ-ፈረንሳይ የድንገተኛ አደጋ ማእከል ለረጅም ጊዜ በፌደራል ስር ሆኖ የቆየ ቢሆንም ከብልፅግና የመንግስት ለውጥ ማግስት በተሰሩት ስራዎች በአስተዳደሩ ስር እንዲሆን መደረጉን ተናግረው ይህም ማእከል ለአጎራባች ክልሎችም ጭምር አገልግሎት የሚሰጥ እንደመሆኑ መጠን የጤና ሚኒስቴር በማእከሉ ውስጥ ሊያስፈልጉ የሚችሉ ድጋፎችን እንዲያደርግ ጠይቀው ለዚህ ማእከል ስኬት የላቀ አስተዋፆ የነበራቸውንም ክቡር ከንቲባው በእለቱ ምስጋናቸውን አቅርበዋል ።
ታሪካዊ የሆነውና ከዚህ ቀደም ምንም አይነት አገልግሎት ሳይሰጥ የቆየውን በአጭር ጊዜ ውስጥ በጤናው መስክ ለነዋሪው ህብረተሰብ አገልግሎት ሊሰጥ በሚችል መልኩ በመሰራቱ የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ከድር ጁሀርና የካቢኔ አባሎቻቸውን የኢ.ፌ.ድ.ሪ የገንዘብ ሚኒስቴር ሚኒስትር ክቡር አቶ አህመድ ሺዴ አመስግነው የድሬዳዋ አስተዳደር ለኢንዱስትሪ ልማት ፣ የሎጅስቲክ ማእከልነት እንዲሁም የሀገራችን የሰላም ማእከል አንዷ እንድትሆን ያደረገው በህዝቦች መካከል ያለው አንድነት እንደሆነና ይህንንም አንድነትና ሰላምና አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባም ክቡር አቶ አህመድ ሺዴ ተናግረዋል ።
በዛሬው እለት ለምረቃ በበቃው ማእከል ውስጥም የኮሮና ቫይረስ ወረርሺኝ በሽታ በድሬዳዋ አስተዳደር በተከሰተበት ወቅት የህክምና አገልግሎት ይሰጥበት እንደነበር የጤና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዲኤታ ዶክተር ደረጄ ዱጉማ ተናግረው ማእከሉ ምቹ ቦታ ላይ እንደመኖሩ መጠን በቀጣይ ሰፊ ስራ በማእከሉ ላይ ከተሰራ በድንገተኛ አደጋና ሌሎች መሰል የጤና መስኮች ላይ በድሬዳዋና በአካባቢው ላሉት የህብረተሰብ ክፍሎች ትልቅ አገልግሎት መስጠት እንደሚቻልም ዶክተር ደረጄ ዱጉማ ተናግረዋል ።
በድሬዳዋ ድልጮራ ሪፈራል ሆስፒታል በ 2014 ዓ.ም ብቻ 12 ሺህ 500 የሚሆኑ ድንገተኛ አደጋ የደረሰባቸውን የህብረተሰብ ክፍሎች አመቺ ባልሆነ መንገድ ህክምና ሲሰጥ መቆየቱን የድሬዳዋ አስተዳደር ጤና ቢሮ ሀላፊ ወ\ሮ ለምለም በዛብህ ተናግረው አገልግሎቱንም ለማሻሻል በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር በተሰጠው እቅድ መሰረት ላለፈው አንድ አመት የተለያዩ ኮሚቴዎችን በማዋቀር የሆስፒታል የቦርድ አመራሮችና የሆስፒታል ማኔጅመንት አባላት ሰፊ ርብርብ በማድረግ ለዛሬው የምርቃ ቀን መብቃቱን ወ\ሮ ለምለም በዛብህ ተናግረዋል ።
በዚሁም የምቃርት ስነ-ስርአት ላይም የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ከድር ጁሀር ፣ የኢ.ፌ.ድ.ሪ የገንዘብ ሚኒስቴር ሚኒስትር ክቡር አቶ አህመድ ሺዴ ፣ የጤና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዲኤታ ዶክተር ደረጄ ዱጉማ ፣ የድሬዳዋ አስተዳደር ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ የተከበሩ ወ\ሮ ፈቲህያ አደን ፣ የድሬዳዋ አስተዳደር ምክትል ከንቲባና የንግድ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ሀላፊ አቶ ሀርቢ ቡህ ፣ የድሬዳዋ ብልፅግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት ሀላፊ አቶ ኢብራሂም ዩሱፍ ፣ ከፍተኛ የመንግስት አመራሮች ፣ የሀይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች ፣ የህክምና ዶክተሮችና የጤና ባለሞያዎች እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል ።
የኢትዮ-ፈረንሳይ የድንገተኛ አደጋ ህክምና ማዕከል እለት ተመረቀ ።


