አሁን ላይ በድሬዳዋ አስተዳደር እየተከናወኑ የሚገኙት የልማት ስራዎች ተስፋ ሰጪ ናቸው” ወደ ድሬዳዋ አስተዳደር የገቡ የሁለተኛ ትውልድ ዲያስፖራዎች

የኢ.ፌ.ድ.ሪ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ(ዶ/ር) የሁለተኛው ትውልድ ኢትዮጲያውያን ዲያስፖራዎች ወደ ሀገር ቤት እንዲገቡ ያስተላለፍትን ጥሪ ተከትሎ ወደ ከተማችን ድሬዳዋ በርካታ ዲያስፖራዎች መምጣታቸው ይታወቃል። በዚህም ወደ ድሬዳዋ አስተዳደር ለመጡ እንግዶች አስተዳደሩ የተለያዩ ሁነቶችን በማዘጋጀት ላይ ሲገኝ ትላንትና ምሽትም በክብር ዶ/ር አሊ ቢራ ፖርክ የድሬዳዋ አስተዳደር ምክትል ከንቲባና የንግድ ኢንድስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኃላፊ የተከበሩ ሀርቢ ቡህ በተገኙበት የእራት ግብዣና የባህል ምሽት ተከናውኗል።

መድረኩን የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት በማስተላለፍ የከፈቱት የድሬዳዋ አስተዳደር ምክትል ከንቲባና የንግድ፣ ኢንደስትሪ እና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኃላፊ ክቡር ሀርቢ ቡህ ሲሆኑ፤ እንደ አስተዳደር ወደ ከተማዋ ለሚመጡ እንግዶች ከታቀዱ ተከታታይ ሁነቶች መካከል ማምሻውን የተከናወነው የእራት ግብዣ አንዱና ዋነኛው መሆኑን ተናግረዋል።

ምክትል ከንቲባው አያይዘውም በቀጣይ የቱሪስት መስህብ ስፍራዎችና የልማት ስራዎች ጉብኝት፣ ኤግዚቢሽንና ባህላዊ እሴቶችን የሚያንፀባርቁ ኪነ ጥበባዊ ዝግጅቶች፣ የህዝብ ውይይት መድረኮች እንዲሁም የኢትዮጵያ ሳምንት ፕሮግራምና ሌሎች ክንውኖች በተያዘላቸው ጊዜ እንደሚከናወኑም ገልፀዋል።

የዲያስፖራው ማህበረሰብ ተሳትፎ የአስተዳደሩን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ከፍታን ስለሚጨምር ብሎሞ የከተማዋን መልካም ገፅታ ለመገንባት በሚደረገው ጥረት የጎላ አስተዋፆ እንዳለውም አቶ ሀርቢ አንስተዋል።

በመጨረሻም ክቡር ከንቲባው ለመላው ዲያስፖራ በአስተዳደር ደረጃ በተለያዩ ጊዜያት የቀረበላቸውን ጥሪ በመቀበል ለአስተዳድሩ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማት ላይ ላሳዩት ተሳትፎ አመስግነዋል፤ በቀጣይም አሁን ላይ እያበረከቱት የሚገኘውን የዕውቀት ሽግግር፣ የገንዘብና የቁሳቁስ ድጋፍ አጠናክራችሁ መቀጠል ይገባቹሀል በማለት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

የድሬዳዋ አስተዳደር የዲያስፖራ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ቢኒያም ግርማ በበኩላቸው የእንግዶች የእንኳን ደህና መጣችሁ የራት ግብዣ ፕሮግራም ያስፈለገው በዋናነት ዲያስፖራዎቹ የኢትዮጵያን የአኗኗር ዘይቤ እንዲያውቁ፣ የሀገር ስሜት ፍቅር እንዲጎለብትባቸው፣ ከሀገራቸው ጋር ያለው ትስስር እንዲዳብርና የቴክኖሎጂ የእውቀት እንዲሁም ሁለንተናዊ ሽግግር እንዲኖር ታስቦ መሆኑን ገልፀዋል።

በመርሀ ግብሩ ላይ ያነጋገርናቸው ዲያስፖራዎች አስተዳደሩ ባደረገላቸው ደማቅ አቀባበል መደሰታቸውን ገልፀዋል። አሁን ላይ በከተማዋ እየተመለከቱት ያለው የልማት ስራዎችም ተስፋ ሰጪ መሆኑን ተናግረዋል። በቀጣይም ለድሬዳዋ እድገት የበኩላቸውን አሻራ ለማኖር ቃል ገብተዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *