የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ፕሮጀክት አፈፃፀም 95 በመቶ መድረሱን የሕዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት አስታውቋል።
ከዚህም ውስጥ የሲቪል ሥራው 98 በመቶ እንዲሁም የኤሌክትሮ ሜካኒካል ሥራው 78 በመቶ መድረሱ ተገልጿል።
የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ መሠረት ድንጋይ የተጣለበት 13ኛ ዓመት “በኅብረት ችለናል!” በሚል መሪ ሃሳብ ይከበራል።
የጽሕፈት ቤቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ፍቅርተ ታምር በሰጡት መግለጫ፤ የግድቡ አጠቃላይ አፈፃፀም 95 በመቶ መድረሱን ገልጸዋል።
የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ሁሉም ኢትዮጵያዊ በሕዳሴ ግድብ ላይ መግባባት የተደረሰበት የከፍታችን ምልክት ነው ብለዋል።
የመሠረት ድንጋይ የተጣለበትን 13ኛ ዓመት በተለያዩ ዝግጅቶች እንደሚከበር ገልፀዋል።
ባለፉት 13 ዓመታት 18 ነጥብ 9 ቢሊየን ብር ከሕዝብ ተሳትፎ ተሰብስቧል ብለዋል።
የመንግሥት ቁርጠኛ አቋምና የዲፕሎማሲ ጥረት እንዲሁም የመላው ኢትዮጵያውያን ድጋፍ ውጤት መሆኑን ገልፀዋል።
የይቻላል መንፈስ የፈነጠቀ ታላቅ ፕሮጀክት መሆኑን ገልፀው፤ በቀጣይም መሰል ፕሮጀክቶችን በተባበረ ክንድ መፈፀም ይገባናል ብለዋል።
በ13ኛው ክብረ-በዓል የቦንድ ሳምንት፣ አውደ-ርዕዮች፣ የምስጋና፣ ዕውቅናና ሌሎች የድጋፍ ማሰባሰብ የንቅናቄ መድረክ ዝግጅቶች እንደሚደረጉ መግለጻቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው።
በቀጣይ የንቅናቄ ዝግጅቶችም 300 ሚሊየን ብር ለማሰባሰብ መታቀዱን ገልፀው፤ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ-ኢትዮጵያውያን ድጋፋቸውን እንዲያጠናክሩ ጥሪ አቅርበዋል ኢቢሲ እንደዘገበው።


