ሀገራዊ ተልዕኮን በአግባቡ የተረዳና በእውቀት የሚመራ የኮሙኒኬሽን እና የህዝብ ግንኙነት ባለሙያን ለመፍጠር የአቅም ግንባታ ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዶክተር ለገሰ ቱሉ ገለጹ፡፡
የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ለፌዴራል እና ለክልል የህዝብ ግንኙነት ኃላፊዎች እና ባለሙያዎች ሲሰጠው የቆየው ስልጠና በዛሬው እለት ተጠናቋል።
የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዶክተር ለገሰ ቱሉ በዚሁ ወቅት እንዳሉት ስልጠናው በአምስት ርእሰ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ነበር።
የመጀመሪያው በአስተሳሳሪ ትርክት ግንባታ ምንነት፣ የሚካሄድባቸው አቅጣጫዎች ቴክኒኮች እና ስልቶች ላይ ያተኮረ ሲሆን ሁለተኛው ቀጣናዊ፣ አህጉራዊ እንዲሁም ዓለም አቀፋዊ ሁኔታዎች ላይ ያተኮረ መሆኑን ጠቁመዋል።
የሰላም ግንባታ ስራዎች እንዲሁም የአስር ዓመቱ የመንግስት የልማት እቅድን ማእከል አድርጎ የተዘጋጀው የሶስት ዓመት የመካከለኛ ዘመን የልማት መርሀ ግብርም የስልጠናው ትኩረት ነበር ብለዋል።
የህዝብ ግንኙነት መሰረታዊ ሃሳቦች እና መሳሪያዎች ትግበራ ሌላኛው ስልጠናው ያተኮረባቸው ርእሰ ጉዳዮች መሆናቸውን ተናግረዋል።
በአጠቃላይ ስልጠናው የዘርፉ ባለሙያዎች ሀገራዊ ተልዕኮዎችን እና የመንግስት ዋና ዋና ትኩረቶች እንዲገነዘቡ እንዲሁም በእውቀት እና በክህሎት የተሟላ አቅም እንዲፈጥሩ ያስቻለ መሆኑን አመላክተዋል።
በቀጣይም በየደረጃው ያለውን ሀገራዊ የመረጃ ፍሰት ለማቀናጀት የዘርፉን ባለሙያዎች አቅም ማጎልበት እንደሚገባ ጠቁመዋል።
በዚህ ረገድ በርካታ የአቅም ግንባታ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸው፥ የኮሙኒኬሽን እና የህዝብ ግንኙነት ባለሙያዎችን አቅም ለማሳደግ የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል።
ለስራው መሳለጥ የሚረዱ አሰራሮች እና መመሪያዎች እየተዘጋጁ መሆኑን እና ሲጠናቀቁ ለዘርፉ ትልቅ እገዛ እንደሚኖረው ጠቁመዋል።
የስልጠናው ተሳታፊዎች በስልጠናው ብዙ ልምድ እና እውቀት ያገኙበት እና ለቀጣይ ስራዎች ስንቅ የሚሆን ትልቅ አቅም የፈጠሩበት መሆኑን ተናግረዋል።
በቀጣይም ከመንግስት ተልእኮዎች እና ዓላማዎች ጋር የተጣጣሙ መልእክቶችን ለህዝብ ለማድረስ እንደሚሰሩ ገልጸዋል።
Ethiopian News Agency


