19ኛው የብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ቀን በድሬዳዋ አስተዳደር “ሀገራዊ መግባባት ለህብረ ብሔራዊ አንድነት” በሚል መሪ በተለያዩ መርሀ ግብሮች እንደሚከበር ተገለፀ::

#DGC ህዳር 3/2017

ዘንድሮ “ሀገራዊ መግባባት ለህብረ ብሔራዊ አንድነት” በሚል ለ19ኛ ጊዜ የሚከበረው የብሄር ብሄረሰቦች ቀን በአስተዳደራችን በተለያዩ መርሀ ግብሮች እንደሚከበርና የማጠቃለያ መርሀ ግብሩም ህዳር 18/2017 ዓ,ም እንደሚደረግ የድሬደዋ አስተዳደር ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ ክብርት ወ/ሮ ፈቲያ አደን ዛሬ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ አስታውቀዋል፡፡

በዚህም የሴቶች፣ የወጣቶች እንዲሁም የሲቪል ሰርቫንት የውይይት መድረክ እንደሚኖር ወ/ሮ ፈቲያ ገልፀው፤ በዓሉ ህብረ ብሄራዊ አንድነትታችንን በማጠናከር የኢትዮጲያ ከፍታ የሚረጋገጥበት መሆኑን ተናግረዋል።

ክብርት አፈ ጉባኤዋ አያይዘውም የዘንድሮ ብሄር ብሄረሰቦች ቀንን ስናከብር ሰው ተኮር ስራዎችን በመስራት መሆኑን አመላክተው በዚህም የደም ልገሳ፣ ማስ ስፖርት እንዲሁም የአቅመ ደከማ ወገኖችን ቤት የማደስ ተግባራት እንደሚከናወኑ ገልፀዋል።

የብልፅግና ፖርቲ 5ኛ አመት የምስረታ በአል እየተከበረ ባለበት ጊዜ ይህ በአል መከበሩ ከዚህ ቀደም ከተከበሩት በዓላት ለየት እንደሚያደርገው ወ/ሮ ፈቲያ ገልፀው፤ ህዝብ ሲጠይቅ የነበረውን የአሳታፊነት ጥያቄ በተመለሰበት ወቅት መከበሩ ልዩ እንደሚያደርገው አብራርተዋል።

አፈ-ጉባዔዋ የብሄር ብሄረሰቦች ቀን የአንድነታችን ዓርማ የሆነው ህገ መንግስታችን የፀደቀበት ቀን በመሆኑ ህብረ ብሄራዊ አንድነታችንን ለማጠናከር ትልቅ ፋይዳ እንዳለው አንስተዋል፡፡ በመጨረሻም ለመላው የአስተዳደራችን ነዋሪዎች የእንኳን አደረሳቹ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

19ኛው የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች ቀን በዋናነት በአርባ ምንጭ ከተማ አዘጋጅነት የሚከበር ይሆናል።

በኤደን ሳሙኤል

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *