የኪነጥበቡ ፌስቲቫሉ መዘጋጀት ዋና አላማ ሠላምን፣ አንድነትን፣ ህብረብሄራዊትን፣ የፍቅርንና መቻቻልን ብሎም ሀገራዊ መግባባትን በኪነጥበቡ ዘርፍ ለማህበረሰቡ ጥልቅ መልዕክት ለማስተላለፍ መሆኑ ተገልጿል።
በድሬደዋ አስተዳደር ወጣቶችና ስፖርት ኮሚሽን የተዘጋጀውና የኮሚሽኑ ታቃፊ የኪነጥበብ ክበባት የተሳተፉበት የኪነጥበብ ፌስቲቫል በሚቀጥሉት ስድስት ወራት በተለያዩ መርሀ ግብሮች በዘጠኙ ቀበሌዎችና በአራቱ ክላስተሮች ተግባራዊ እንደሚሆን ተጠቁሟል።
በኪነጥበቡ ማስጀመሪያ መርሀ ግብር ላይ በመገኘት ንግግር ያደረጉት የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ከድር ጁሀር ወጣቶች ሀገር ተረካቢ ትውልድ እንደመሆናቸው ከጥላቻና ግለኝነት አስተሳሰብ በመራቅ ፍቅርንና አንድነትን ብሎም ህብረብሄራዊ መግባባትን ማቀንቀን ባህል ማድረግ አለባቸው ብለዋል።
ክቡር ከንቲባው አክለውም ኢትዮጵያ የወደፊት ብሩህ ተስፋዋን እንድትጨብጥ ሁላችንም በአንድነት መረባረብ ይገባናል ብለው በኪነጥበብ ዘርፉም በተለይ የሠላም እሴት ተበክሮ መሰበክ እንዳለበት አስገንዝበዋል።
ድሬደዋ የሠላምና የፍቅር ተምሳሌትነቷ መገለጫዋ የሆነው ነዋሪዎቿ ባሳዩት አንድነታዊ መግባባት ነው ብለው ወጣቶችም ይህን የቆየ የከተማዋን እሴት አጠናክረው ማስቀጠል አለባችሁ ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
የድሬደዋ አስተዳደር ወጣቶችና ስፖርት ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ካሊድ መሀመድ በበኩላቸው ድሬደዋ ወትሮም ለጥበቡ ዘርፍ አዲስ አለመሆኗን ገለፀው ዘርፉ ያለውን ተሠሚነት በመጠቀም የሠላምና የአብሮነትን እሴት ለመስበክ የኪነጥበብ የፌስቲቫሉ መዘጋጀቱን ገልጸዋል።
ኮሚሽነሩ አክለውም በሚቀጥሉት ስድስት ወራት በሚቆየው የኪነጥበብ ፌስቲቫል ከሠላም እሴት በተጨማሪ በኤች አይ ቪ፣ በስነ ተዋልዶና በመጤ ባህሎችና ጎጂነታቸው ዙሪያ ጠንካራና ጥልቅ ሃሳቦች ለማህበረሰቡ እንደሚተላለፉበት አመልክተዋል።
የኪነጥበቡ ዘርፍንም እንደ ድሬዳዋ ለማሳደግ ፌስቲቫሉ ትልቅ ጠቀሜታ እንደሚኖረው ገልጸው ወደፊትም በዘርፉ ተሠጥኦ ያላቸውን ወጣቶች ለማብቃት መሰል ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል።
በመርሀ ግብሩ ላይ በአስተዳደሩ ወጣቶችና ስፓርት ኮሚሽን ስር የሚገኙ የኪነጥበብና ሰርከስ ክበባቶች አስተማሪና አዝናኝ ትዕይንቶችን ያቀረቡ ሲሆን ለሁለት ቀናት ያህል በድሬዳዋ ተካሂዶ በነበረው የሠላም ኮንፍረንስ አስተዋጽኦ ላበረከቱ አካላት የዕውቅና ሰርተፊኬት ተበርክቷል።


