የመክፈቻ ውድድሩ በማውንቴን ብስክሌት ታዳጊ የፕሮጄክት ተወዳዳሪዎች 15.4 ኪ/ሜትር በሚሸፍን የ7 ዙር ውድድር የተጀመረ ሲሆን ይሳኮር ፍሬው፣ አቤኔዘር አለሙ እና ምህረት ሞገስ ከአንድ እስከ ሶስት በመውጣት ውድድራቸውን አጠናቅቀዋል፡፡
በሰላሳ ስድስት ዙሮች 79.2 ኪ/ሜትር በሚሸፍነው ውድድር በቅርቡ የተመሰረተው ቶቶ ብስክሌት ክለብን ጨምሮ፣ ድሬዳዋ ከነማ፣ ድሬዳዋ ፖሊስ፣ ማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ፣ አዲስ አበባ እና የትግራዮ ወልዋሎ አዲግራት አዲ መድሃኒት ፋብሪካ ብስክሌት ክለቦች ሰላሳ ስድስት ብስክሌተኞች የተሳተፉበትና የስፖር አፍቃሪውን ቀልብ የገዛ ጠንካራ ፉክክር የተደረገበት ውድድር በድሬ ዳዋ ከተማ ከዚራ ጎዳና ላይ በርካታ ተመልካቾች ተከታትለውታል፡፡
በመጀመሪያው ቀን ውድድር የትራዩ ወልዋሎ አዲግራት አዲስ መድሃኒት ፋብሪካ ብስክሌት ቡድን በግልና በቡድን አንደኛ በመሆን ያጠናቀቀ ሲሆን በግል አብይ አለም መብርሃቱ 1ኛሲወጣ በቡድንም 4፡32፡28፡29 ሰዓት በማስመዝገብ ወልዋሎ ቀዳሚ ሊሆን ችሏል፡፡ በግል ኃይለ መለኮት የቡድኑን ልጅ ተከትሎ 2ኛ ሲወጣ በቅርቡ በአቶ ቢኒያም ነገሰ የተመሰረተው ቶቶ ብስክሌት ቡድን ተወዳዳሪው ኪያ ጀማል 3ኛ ሆኖ ውድድሩን አጠናቋል፡፡
በቡድን በሴኮንዶች ልዩነት 4፡32፡34፡29 ሰዓት በማስመዝገብ ቶቶ ብስክሌት ክለብ 2ኛ ፣ በ4፡32፡50፡ 39 ድሬዳዋ ከነማ 3ኛ ሆነዋል፡፡
በ36 ዙሮች 79.2 ኪ/ሜትር በሸፈነው በዚህ የመጀመሪያው ቀን የብክሌተ ውድድር 12 ብስክሌተኞች ተደርበው ከውድድሩ ውጪ ሲሆኑ 24 ተወዳዳሪዎች ለቀጣዩ ዙር ማለፍ ችለዋል ፡፡
በርካታ ዙሮችን አስከ መጨረሻው ዙር ድረስ ከፊት ሲመራ የቆየው የድሬዳዋ ከነማ ብስክሌት ቡድን ተወዳዳሪው ይትባረክ ታጀበ ዙሩን ሊጨርስ ከመቶ ሜትር ያነሰ ርቀት ሲቀረው ወድቆ በመንሸራተት አምስተኛ ደረጃን ይዞ ያጠናቀቀበት ሁኔታ በስፖርት ቤተሰቡ ዘንድ ቁጭትና ደስታን የፈጠረ የውድድሩ ክስተት ነበር፡፡
ሀሪፍ ድሬ ሀገር አቀፍ ውድድር በድሬዳዋ ከተማ መጀመሩ የድሬዳዋንም ሆነ በሀገራቀፍ ደረጃ መቀዛቀዝ የሚታይበትን የብስክሌት ስፖርት ዳግመኛ እንዲነቃቃ ፣ አዳዲስ ጠንካራ ብስክሌተኞች እና ክለቦች የሚፈሩበትን እድል ይዞ ሊመጣ የሚችል ነው የሚል ተስፋ እንዲሰንቁ ያደረጋቸው መሆኑን ውድድሩን የታደሙ የስፖርቱ አፍቃሪያን አስተያየታቸውን ሰጥተዋል ፡፡
በተለይም የተለያዩ ድርጅቶችና ተቋማት እንደዚሁም ፋብሪካዎች ማህበራዊ ኃላፊነታቸውን ከመወጣት አኳያ የብስክሌት ክለቦችን በማቋቋም ለስፖርቱ መነቃቃትና እድገት የበኩላቸውን ድርሻ ሊወስዱ እንደሚገባም ነው የስፖርቱ አፍቃሪን በአስተያየታቸው የገለጹት፡፡
ከፍተኛ ወጪ በማውጣ ዘመናዊ የውድድር ብስክሌቶችን ገዝተው ቶቶ የብስክሌት ክለብን ከማቋቋም ባለፈ እንዲህ አይነት የተመልካቹን ቀልብ መግዛት የቻለ አጓጊ ፉክክር የታየበትን ደማቅ ሀገራቀፍ ዝግጅት ከኢትዮጵያ ብስክሌተ ፌዴሬሽን ጋር በመተባበር የምንወደውን የስፖርት ውድድር እንድንመለከት ላስቻሉን የድሬ ቱዩብ እና ሀሪፍ ስፖርት አገልግሎት ኃላፊነቱ የተወሰነ ድርጅት ባለቤት አቶ ቢኒያም ነገሰ ምስጋና ይገባቸዋል ያሉት አስተያየት ሰጪዎቹ ሌሎች ባለሀብቶችም ለስፖርቱ እድገት ፈለጋቸውን ሊከተሉ ይገባል ሲሉ ጠቁመዋል፡፡
በዳንኤል አማረ
ፎቶ፦አገኘሁ ሸዋረጋ


