ሄር ኢሴ” የሶማሌ ኢሳ ማህበረሰብ ባህላዊ የዳኝነት ስነ-ስርዓት በዩኒስኮ መመዝገቡን ተከትሎ የድሬዳዋ ዩኒቨርስቲ በዛሬው ዕለት የግንዛቤ ማስጨበጫና የውይይት መድረክ አካሄደ

በዚህም በመድረኩ የተገኙት የድሬዳዋ ዩኒቨርስቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ኡባ አደም የሄር ኢሴ የሶማሌ ኢሳ ማህበረሰብ ያልተፃፈ ባህላዊ ህግ በሰው ልጆች ወካይ አለም አቀፍ የማይዳሰስ ቅርስነት በመመዝገቡ የተሰማቸውን ደስታ ገልፀዋል፡፡

ዶ/ር ኡባ አያይዘውም የማንነታችን መገለጫ የሆኑ የራሳችንን ባህሎች ማደበር እንደሚገባ ተናግረው፤ የድሬዳዋ ዩኒቨርስቲም እንደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋም ለሀገር በቀል እውቀት ትኩረት ሰቶ እየሰራ እንደሚገን ገልፀዋል፤ በቀጣይም በሄር ኢሴ ላይ የተለያዩ የግንዛቤ መፍጠሪያ ስራዎችን ጨምሮ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላቶች ጋር በጋራ በመሆን የተለያዩ ስራዎች እንደሚሰሩ ተጠቁመዋል ፡፡

ሀገራችን ኢትዮጲያ የበርካታ ባህልና እሴቶች ባለቤት መሆኗን የተናገሩት ዶ/ር ኡባ ”ሄር ኢሴ“ ከ5 መቶ አመታት በላይ ያስቆጠረና አባቶቻችን ጠብቀው ያቆዩልን ባህላዊ ግጭቶችን መፍቻ መሆኑን አመላክተዋል፡፡

እኛም ከአባቶቻችን የተረከብነውን ጠብቀን ለቀጣይ ትውልድ የማሸጋገር ሀላፊነት አለብን ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

ሄር ኢሴ ባህላዊ የዳኝነት ስርአት በዩኔስኮ እንዲመዘገብ 3ቱ ሀገራት ማለትም ኢትዮጲያ፣ ጅቡቲና ሶማሊያ በጋራ በርካታ ስራዎቹን እንዳከናወኑ ዶ/ር ኡባ በመጠቆም፤ ለዚህም የበኩላቸውን አስተዋፆ ላበረከቱ አካላት ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡

በኤደን ሳሙኤል

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *