በድሬዳዋ እየተካሔደ ባለው የድሬ ሀሪፍ ሀገር አቀፍ የሳይክል ሻምፒዮና በሁለተኛው ዙር ውድድር የወልዋሎ አዲግራት አዲስ መድሃኒት ፋብሪካ ተወዳዳሪው ኃይለመለኮት ወልደ አብእዝጊ አንደኛ በመውጣት አጠናቅቋል።

የሁለተኛው ዙር ውድድር በድሬዳዋ አስተዳደር የከንቲባ ጽ/ቤት ህንፃ ፊትለፊት መነሻና መድረሻውን አድርጎ በ29 ዙሮች የአንድ መቶ ኪ/ሜትር እርቀት የሸፈነ ሲሆን ከስድስት የብስክሌት ክለቦች የተውጣጡ ተወዳዳሪዎች ጠንካራ ፉክከር አድርገውበታል።

በውድድሩ አንደኛ ሆኖ ያጠናቀቀው ኃለመለኮት ወልደ አብእዝጊ ስለውድድሩ በሰጠው አስተያየት ጠንካራ ፉክክር የተደረገበት መሆኑን ጠቅሶ በተለይ የድሬዳዋ ብስክሌት አፍቃሪው ተመልካች ለስፖርቱ ያለው የተለየ ፍቅር ለተወዳዳሪዎችም ልዩ ሞራል የሚሰጥ ነው ብለዋል።

የድሬዳዋ አስተዳደር የሳይክል ስፖርት እንዲጠናከር የሚያደርገው እንቅስቃሴ ለሌሎችም በአርዓያነት የሚጠቀስ ነው ያለው ኃይለመለኮት በዛሬው ውድድር የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ክቡር አቶ ከዲር ጁሐር ተወዳዳሪዎችን በሞተር ሳይክል ከፊት እየመሩ ውድድሩን መምራታቸው ልዩ ስሜት የሚሰጥ እና የድሬዳዋን ፍቅርና የሰላም ከተማነት ማሳያ ነው ብሏል፡

በቅርቡ የጠቋቋመው ቶቶ የሳይክል ክለብ ተወዳዳሪው አሚር ጃፋር ውድድሩን ሁለተኛ ሆኖ አጠናቅቋል። አሚር በውድድሩ ማጠናቀቂያ ላይ በሠጠው አስተያየት የአስተዳደሩ ከንቲባ ክቡር አቶ ከድር ጁሐር የሁለተኛውን ዙር ውድድር በሞተር አጅበው መምራታቸው ለተወዳዳሪዎች ልዩ ሞራል የሚሰጥ መሆኑን አንስቶ ስፖርቱን በመደገፍ ረገድ በአርዓያነት የሚነሱ ናቸው ብሏል።

አሚር የቶቶ የሳይክል ክለብን ከመመሰረት አንስተው ይህ ውድድር እንዲካሔድ ከኢትዮጵያ ብስክሌት ፌዴሬሽን ጋር በመተባባር ያዘጋጁት አቶ ቢኒያም ነገሱን ከዚህ የተሻለ ውጤት በማስመዝገብ የልፋታቸውን ፍሬ እንዲመለከቱ ጠንክረን እንሰራለን ብሏል።

ውድድሩን ሶተኛ በመሆን ያጠናቀቀው የድሬዳዋ ከነማ ብስክሌት ክለብ ተወዳዳሪው አክረም ከድር ነው ። አክረም በውድድሩ ማብቂያ ላይ በሰጠው አስተያየትም ውድድሩን በበላይነት ለማጠናቀቅ ወስኖ መጀመሩን ያወሳ ሲሆን በተለይም በውድድሩ የአስተዳደሩ ከንቲባ ስፖርቱ እንዲጠናከር የድሬዳዋ ከነማ ብስክሌት ቡድን ዘመናዊ ሳይክሎችን በመግዛትና በመደገፍ እያደረጉት ያለውን አስተዋጾ የሚያስመሰግናቸው መሆኑን ገልጾ ፣ ውድድሩን አጅበው ተጫዋቾችን ማበረታታቸው ደግሞ እኛም የተሸለ ውጤት እንድናስመዘግብ ብርታትና ሞራል ሆኖናል ነው ያለው፡፡

ከታህሳስ 26 እስከ ጥር 4 በሚካሔደው ድሬ ሀሪፍ አገራቀፍ የብስክሌት ሻምፒዮና ውድድር ቀጣይ ጫወታ በድሬዳዋ ነጻ የንግድ ቀጠና አካባቢ የፊታችን ሃሙስ የሰዓት የግል ውድድር የሚካሔድበት ሲሆን እሁድ በከዚራ የፍጻሜ ውድድር የሚካሔድ መሆኑን የወጣው የውድድሩ መርሃ ግብር ያሳያል ።

በዳንኤል አማረ

ምስል: ፍፁም

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *