የድሬዳዋ አስተዳደር ፍትህ፣ ፀጥታና ህግ ጉዳዮች ቢሮ ከአስተዳደሩ 38 የገጠር ቀበሌዎች ለተውጣጡ የሚኒሻ ሀይል አባላት ከጥር 1 እስከ 15 /2017 ዓ.ም ሲሰጥ የቆየውን የአቅም ማጎልበቻ ስልጠና ያጠናቀቁ አባላትን በዛሬው ዕለት በድምቀት አስመርቋል።.
በምርቃት መርሀ ግብሩ የተገኙት የድሬዳዋ አስተዳደር ክቡር ከንቲባ አቶ ከድር ጁሀር ለተመራቂዎች የእንኳን ደስ አላችሁ መልእክታቸውን በማስተላለፍ፤ 1 ሺ 7 መቶ አርባ አምስት ነባር እና አዲስ የሚሊሻ አባላት ለ 15 ቀናት የአቅም ማጎልበቻ ስልጠና መውሰዳቸውን ተናግረዋል።
ከንቲባ ከድር አያይዘውም በስልጠናው ተግባር ተኮርና የንድፈ ሀሳብ እንዲሁም በመስክ ወታደራዊ ስልቶች ላይ ስልጠናው መሰጠቱን ጠቁመዋል።
በመጨረሻም በምትሰማሩበት ቦታ ሁሉ ሀላፊነታችሁን በአግባቡ በመወጣትና በሚሊሻ ዲሲፒሊን በመመራት አካባቢያችሁን ከፀረ ሰላም ሀይሎች እና ወንጀል ፈፃሚዎች በመከላከል አስተዳደራችንን ከወንጀል የጸዳ ሠላምና ፀጥታ የሰፈነበት ለልማትና ለሥራ ምቹ የማድረግ ኃላፊነታችሁን እንድትወጡ ሲሉ ክቡር ከንቲባ ከድር ለተመራቂዎች መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
የድሬዳዋ አስተዳደር ፍትህ፣ ፀጥታና ህግ ጉዳዮች ቢሮ ሀላፊ አቶ አብዱሰላም አህመድ በበኩላቸው
የዛሬ የአስተዳደራችን ተመራቂ የሚኒሻ ሀይል አባላት በዋነኝነት የአካባቢውን ህብረተሰብ ፀጥታ የማስከበር፣ የመሰረተ ልማት አውታሮችን ከፀረ-ሰላም ሃይሎች የመጠበቅ፣ ህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርን ጨምሮ የጦር መሳሪያ ዝውውርና ኮትሮባንድን የመከላከልና የፀጥታ ተግባራትን እንደሚያከናውኑ እንዲሁም በሚኖሩባቸው አካባቢዎችም አልፎ አልፎ በማህበረሰቡ ዉሰጥ የሚፈጠሩ አለመግባበቶችን ወደ ግጭት አንዳያመሩ በመፍታትና ከአጎራባች ወረዳዎች ጋር የቅርብ ግንኙነቶችን በመፍጠር ሰላምን በማፅናት እረገድ ትልቅ ሚናን እንደሚጫወቱ ጠቁመዋል።
ስልጣኞች የወሰዳችሁትን ስልጠና ወደ ተገባር በመቀየር የሚጠበቅባችሁን ሀላፊነት መወጣት ይጠበቅባቹሀል ሲሉም አቶ አብዱ ሰላም ተናግረዋል።
ተመራቂዎች በበኩላቸው በስልጠና ቆይታቸው በርካታ እውቀቶችን እንዳገኙ ተናግረው የሚጠበቅባቸውን ሀላፊነት ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን ገልፀዋል።
በኤደን ሳሙኤል
ፎቶ:-ረመዳን አደም


