በዘንድሮ የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ስራ 11 ሺ አባወራዎችን ተጠቃሚ ለማድረግ ታስቧል::

በድሬዳዋ አስተዳደር በአሰሊሶ ክላስተር ለገዶን ገጠር ቀበሌ “የአፈር ሀብታችን ለብልፅግናችን” በሚል የ2017 ዓ.ም የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ስራ መክፈቻ መርሀ ግብር ተካሄደ።

በመርሀ ግብሩ የተገኙት የድሬዳዋ አስተዳደር ብልጽግና ፓርቲ ቅ/ጽፈት ቤት ምክትልና የፖለቲካ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ሻኪር አህመድ ባለፉት አመታት በህዝብ ንቅናቄ በተሰሩ የተፋሰስ ልማት ስራዎች ከ50 ሺ ሄክታር በላይ መሬትን ማልማት እንደተቻለ፤ እንዲሁም የአፈር ለምነትን ማሻሻልና የጎርፍና የድርቅ ተጋላጭነትን መቀነስ እንደተቻለ ጠቁመዋል።

አቶ ሻኪር አያይዘውም በእንሰሳትና ሰብል ልማት ከፍተኛ እድገት እንደተመዘገበም ገልፀዋል።

ዛሬ በተጀመረውና ለ30 ቀናት በሚዘልቀው የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ሥራ 5 ሺህ 550 ሄክታር መሬት ላይ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራዎችን በማከናወን 3.7 በመቶ የመሬት መራቆትን በመቀነስ በየአመቱ በጎርፍ ሊወሰድ የሚችለውን 48 ሺ 685 ቶን ለም አፈርን ለመታደግ መታቀዱን አቶ ሻኪር ተናግረዋል።

በዘንድሮ የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ስራ የትምህርት፣ የጤና፣ የመስኖ ውሃና የማሳ እንክብካቤ ተግባራትን ከፍ የሚያደርጉ ስራዎች እንደሚተገበሩ ተመላክቷል።

በመጨረሻም አቶ ሻኪር ህብረተሰቡ በነቂስ ወጥቶ በልማቱ ላይ በመሳተፉ አመስግነው፤ በቀጣይም ተጠናክሮ እንዲቀጥል መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

በኤደን ሳሙኤል

ፎቶ:-ሰላም አበበ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *